2 ጴጥሮስ 2 NASV

ሐሰተኛ መምህራንና መጨረሻቸው

1 ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት በሕዝቡ መካከል እንደ ነበሩ እንዲሁም በእናንተ መካከል ሐሰተኞች መምህራን ይነሣሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው ጥፋት የሚያስከትል የስሕተት ትምህርት በስውር ያስገባሉ፤ በዚህም በራሳቸው ላይ ድንገተኛ ጥፋት ያመጣሉ።

2 ብዙዎች አስነዋሪ ድር ጊቶቻቸውን ይከተላሉ፤ በእነርሱም ምክንያት የእውነት መንገድ ይሰደባል።

3 እነዚህ ሐሰተኞች መምህራን እየተስገበገቡ በፈጠራ ታሪካቸው ይበዘብዙዋችኋል። ፍርዳቸው ከጥንት ጀምሮ ዝግጁ ነው፤ መጥፊያቸውም አያንቀላፋም።

4 እግዚአብሔር ኀጢአት የሠሩትን መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ከጣላቸውና በጨለማ ጒድጓድ ውስጥ ለፍርድ ካስቀመጣቸው፣

5 የጽድቅ ሰባኪ የነበረውንም ኖኅን ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር አድኖ ለቀድሞው ዓለም ሳይራራ በኀጢአተኞች ላይ የጥፋት ውሃ ካመጣ፣

6 ደግሞም ኀጢአት ለሚያደርጉ ሁሉ ምሳሌ እንዲሆኑ የሰዶምንና የገሞራን ከተሞች ዐመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጥሎ ከፈረደባቸው፣

7 ጻድቅ የሆነውንና በዐመፀኞች ሴሰኛ ድርጊት እየተሣቀቀ የኖረውን ሎጥን ካዳነ፣

8 ያ ጻድቅ ሰው በእነርሱ መካከል ሲኖር በሚያየውና በሚሰማው ነገር ነፍሱ ዕለት ዕለት በዐመፀኛ ድርጊታቸው ብትጨነቅም፣

9 ጌታ፣ በእውነት እያመለኩት የሚኖሩትን ከፈተና እንዴት እንደሚያድናቸውና ዐመፀኞችን እየቀጣ ለፍርድ ቀን እንዴት ጠብቆ እንደሚያቈያቸው ያውቃል።

10 በተለይም በርኩስ ምኞት የሥጋ ፍላጎታቸውን የሚከተሉትንና ሥልጣንን የሚንቁትን ለፍርድ ጠብቆ ያቈያቸዋል።እነዚህ ሰዎች ደፋሮችና እብሪተኞች ስለሆኑ ሰማያውያንን ፍጡራን ሲሳደቡ አይፈሩም፤

11 ነገር ግን መላእክት ከእነርሱ ይልቅ ብርቱና ኀያል ሆነው ሳሉ፣ በጌታ ፊት በእነርሱ ላይ የስድብ ቃል አይሰነዝሩም።

12 እነዚህ ሰዎች ግን ምንም በማያውቁት ነገር እየገቡ ይሳደባሉ፤ እነርሱም ለመያዝና ለመገደል እንደ ተወለዱ፣ በስሜታቸው ብቻ እንደሚመሩና ልቦናም እንደሌላቸው አራዊት ናቸው፤ የሚጠፉትም እንደ እንስሳት ነው።

13 ለዐመፃቸው የሚገባውን የዐመፅ ዋጋ ይቀበላሉ፤ በጠራራ ፀሓይ ሲፈነጥዙ እንደ ደስታ ይቈጥሩታል፤ በግብዣ ላይ ሳሉ ነውረኞችና ርኩሶች ሆነው ከእናንተም ጋር በፍቅር ግብዣ ላይ ይቀመጣሉ፤

14 ዐይናቸው ቅንዝር የተሞላ በመሆኑ ኀጢአትን ከመሥራት አይቈጠቡም፤ ጽኑ ያልሆኑትን ነፍሳት ያስታሉ፤ ስስትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው!

15 ቀናውን መንገድ ትተው፣ የዐመፅን ደመወዝ የወደደውን የቢዖርን ልጅ የበለዓምን መንገድ ተከትለው ስተዋል፤

16 እርሱ ግን ስለ መተላለፉ ተገሥጾአል፤ መናገር የማይችል አህያ በሰው ቋንቋ ተናግሮ የነቢዩን እብደት ገታ።

17 እነዚህ ሰዎች የደረቁ ምንጮችና በዐውሎ ነፋስ የሚነዱ ደመናዎች ናቸው፤ የሚጠብቃቸውም ድቅድቅ ጨለማ ነው፤

18 ከንቱ ቃል እየደረደሩ በስሕተት ከሚኖሩት መካከል አምልጠው የመጡትን ሰዎች በሴሰኛ ሥጋዊ ምኞት በማባበል ያታልላሉና።

19 እነርሱ ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው ሳሉ፣ ሌሎችን ነጻ ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጧቸዋል፤ ሰው ለተገዛለት ለዚያ ነገር ባሪያ ነውና።

20 ጌታችንንና አዳኛችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቅ ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ እንደ ገና ተጠላልፈው ቢሸነፉ ከመጀመሪያው ይልቅ የኋለኛው ሁኔታቸው የከፋ ይሆንባቸዋል።

21 የጽድቅን መንገድ ካወቁ በኋላ ከተሰጣቸው ቅዱስ ትእዛዝ ወደ ኋላ ከሚመለሱ፣ ቀድሞውኑ የጽድቅን መንገድ ባላወቁዋት ይሻላቸው ነበር።

22 “ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል” እንዲሁም “ዐሣማ ቢታጠብም ተመልሶ በጭቃ ላይ ይንከባለላል” የሚለው ምሳሌ እውን ይሆንባቸዋል።

ምዕራፎች

1 2 3