ማቴዎስ 12:41-47 NASV

41 የነነዌ ሰዎች በፍርድ ዕለት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና። እነሆ፤ ከዮናስ የሚበልጥ እዚህ አለ።

42 በፍርድ ዕለት የደቡብ ንግሥት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ መጥታለችና። እነሆ፤ ከሰሎሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።

43 “ርኩስ መንፈስ ከሰው ከወጣ በኋላ ዕረፍት ለማግኘት ውሃ በሌለበት ደረቅ ቦታ ይንከራተታል፤ የሚሻውን ዕረፍት ግን አያገኝም።

44 ከዚያም፣ ‘ወደ ነበርሁበት ቤት ተመልሼ ልሂድ’ ይላል፤ ሲመለስም ቤቱ ባዶ ሆኖ፣ ጸድቶና ተዘጋጅቶ ያገኘዋል።

45 ከዚያም ይሄድና ከራሱ የባሱ ሌሎች ሰባት ክፉ መናፍስት ይዞ ይመጣል፤ እነርሱም ሰውየው ውስጥ ገብተው ይኖራሉ። የዚያም ሰው የኋለኛው ሁኔታ ከፊተኛው የከፋ ይሆናል። በዚህ ክፉ ትውልድም ላይ እንዲሁ ይሆንበታል።”

46 ኢየሱስ ለሕዝቡ ሲናገር ሳለ፣ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር።

47 አንድ ሰውም፣ “እነሆ፣ እናትህና ወንድሞችህ ሊያነጋግሩህ ፈልገው በውጭ ቆመዋል” አለው።