8 ሌላው ዘር ደግሞ በጥሩ መሬት ላይ ወደቀ፤ ፍሬም አፈራ፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ሥልሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ።
9 ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!”።
10 ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ለምን ለሕዝቡ በምሳሌ ትናገራለህ?” አሉት።
11 እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “ለእናንተ የመንግሥተ ሰማይን ምስጢር ማወቅ ተሰጥቶአችኋል፤ ለእነርሱ ግን አልተሰጣቸውም።
12 ላለው ይጨመርለታል፤ ይበዛለትማል፤ ከሌለው ግን ያ ያለው እንኳ ይወሰድበታል።
13 ስለዚህ እንዲህ በማለት በምሳሌ የምነግራቸው ለዚህ ነው፤ “እያዩ ስለማያዩ፣ እየሰሙ ስለማይሰሙ ወይም ስለማያስተውሉ ነው።
14 እንዲህ ተብሎ የተነገረው የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል፤ “ ‘መስማትንስ ትሰማላችሁ፤ ነገር ግን አታስተውሉም፤ ማየትንም ታያላችሁ፤ ነገር ግን ልብ አትሉም።