ማቴዎስ 16:19-25 NASV

19 የመንግሥተ ሰማይን መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር ያሰርኸው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤ በምድርም የፈታኸው ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል።”

20 ቀጥሎም እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ለማንም እንዳይናገሩ ደቀ መዛሙርቱን አስጠነቀቃቸው።

21 ኢየሱስ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ፣ በዚያም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በኦሪት ሕግ መምህራን እጅ መከራን ይቀበልና ይገደል ዘንድ፣ በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣ ዘንድ እንደሚገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጽላቸው ጀመር።

22 ጴጥሮስም ኢየሱስን ወደ ጐን ሳብ አድርጎ፣ “ጌታ ሆይ፤ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይድረስብህ” እያለ ይገሥጸው ጀመር።

23 ኢየሱስም ወደ ጴጥሮስ ዘወር ብሎ፣ “አንተ ሰይጣን፣ ሂድ ከዚህ! የሰው እንጂ የእግዚአብሔር ነገር በሐሳብህ ስለሌለ መሰናክል ሆነህብኛል!” አለው።

24 ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፤ “ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ፤

25 ነፍሱን ሊያድን የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነገር ግን ነፍሱን ስለ እኔ የሚያጠፋት ያድናታል።