ማቴዎስ 19:23-29 NASV

23 ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፣ ለሀብታም ወደ መንግሥተ ሰማይ መግባት እጅግ አስቸጋሪ ነው።

24 ደግሜ እላችኋለሁ፤ ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀላል።”

25 ይህን ሲሰሙ፣ ደቀ መዛሙርቱ እጅግ በመገረም፣ “እንግዲያስ ማን ሊድን ይችላል?” ሲሉ ጠየቁ።

26 ኢየሱስም እየተመለከታቸው፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉም ነገር ይቻላል” አላቸው።

27 ጴጥሮስም መልሶ፣ “እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል፤ ታዲያ ምን እናገኝ ይሆን?” አለው።

28 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ በሚመጣው አዲስ ዓለም የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበት ጊዜ፣ እናንተም የተከተላችሁኝ በዐሥራ ሁለት ዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ ትፈርዳላችሁ።

29 ስለ ስሜ ብሎ ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ አባትን፣ እናትን ፣ ልጆችን ወይም ዕርሻን የሚተው ሁሉ መቶ ዕጥፍ ይቀበላል፤ የዘላለምንም ሕይወት ይወርሳል።