20 እርሱም፣ “በዚህ ገንዘብ ላይ የሚታየው መልክ የማን ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው።
21 እነርሱም፣ “የቄሣር ነው” አሉት።እርሱም መልሶ፣ “እንግዲያውስ የቄሣርን ለቄሣር፣ የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው።
22 ይህን ሲሰሙ ተደነቁ፤ ትተውትም ሄዱ።
23 የሙታን ትንሣኤ የለም ብለው የሚያምኑ ሰዱቃውያን በዚያኑ ቀን ወደ ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ ብለው ጠየቁት፤
24 “መምህር ሆይ፤ ሙሴ፣ ‘አንድ ሰው ከሚስቱ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ወንድሙ የሟቹን ሚስት አግብቶ ለእርሱ ዘር ይተካለት’ ብሎአል።
25 በእኛ ዘንድ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ በመሞቱ፣ ሚስቱን ወንድሙ አገባት፤
26 እንደዚሁ ደግሞ ሁለተኛውም፣ ሦስተኛውም እስከ ሰባተኛው ድረስ በዚህ ሁኔታ ሞቱ።