1 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ባሕሩን በጀልባ ተሻግሮ ወደ ራሱ ከተማ መጣ።
2 በዚያም ሰዎች አንድ ሽባ ሰው በቃሬዛ ተሸክመው ወደ እርሱ አመጡ። ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን፣ “አይዞህ አንተ ልጅ፤ ኀጢአትህ ተሰርዮልሃል” አለው።
3 በዚህን ጊዜ የአይሁድ ሃይማኖት መምህራን፣ “ይህማ እግዚአብሔርን መሳደብ ነው” በማለት በልባቸው አጕረመረሙ።
4 ኢየሱስ ሐሳባቸውን ተረድቶ እንዲህ አለ፤ “ክፉ ነገር በልባችሁ ለምን ታስባላችሁ?
5 ለመሆኑ፣ ‘ኀጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል’ ከማለትና ‘ተነሥተህ ሂድ’ ከማለት የቱ ይቀላል?
6 ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኀጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን እንዳለው እንድታውቁ ነው’ ብሎ፣ ሽባውን፣ ‘ተነሣ! ቃሬዛህን ይዘህ ወደ ቤትህ ሂድ’ ” አለው።