ማቴዎስ 9:8-14 NASV

8 ሕዝቡም ይህን ባዩ ጊዜ ተደነቁ፣ በፍርሃት ተሞልተው፣ እንደዚህ ያለ ሥልጣን ለሰው የሰጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

9 ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ሲሄድ ማቴዎስ የሚባል አንድ ሰው በቀረጥ ማስከፈያ ኬላ ተቀምጦ አየ፤ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው።

10 ኢየሱስ በማቴዎስ ቤት በማእድ ላይ ሳለ፣ ብዙ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ኀጢአተኞች መጥተው ከእርሱና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር አብረው ሊበሉ ተቀመጡ።

11 ፈሪሳውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን፣ “መምህራችሁ ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኀጢአተኞች ጋር እንዴት አብሮ ይበላል?” ብለው ጠየቋቸው።

12 ኢየሱስም የተናገሩትን ሰምቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሐኪም የሚያስፈልገው ለሕመምተኞች እንጂ ለጤነኞች አይደለም፤

13 ሄዳችሁ፣ ‘ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤’ የሚለውን ቃል ትርጕም አጢኑ፤ ኀጢአተኞችን እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና።”

14 የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ወደ ኢየሱስ ቀርበው፣ “እኛና ፈሪሳውያን ስንጾም፣ ያንተ ደቀ መዛሙርት ግን ለምን አይጾሙም?” ብለው ጠየቁት።