ዕብራውያን 9:6-12 NASV

6 ሁሉም በዚህ መልክ ከተዘጋጀ በኋላ፣ ካህናት አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ዘወትር ወደ ድንኳኒቱ መጀመሪያ ክፍል ይገባሉ።

7 ነገር ግን ወደ ውስጠኛው ክፍል የሚገባው ሊቀ ካህናቱ ብቻ ነበር፤ የሚገባውም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን፣ ስለ ራሱ ኀጢአትና ሕዝቡ ባለማወቅ ስላደረገው ኀጢአት የሚያቀርበውን ደም ሳይዝ ከቶ አይገባም ነበር።

8 የመጀመሪያዪቱ ድንኳን ቆማ እስካለች ድረስ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የሚወስደው መንገድ ገና እንዳልተገለጠ መንፈስ ቅዱስ ያሳያል።

9 ይህም ለአሁኑ ዘመን ምሳሌ ሲሆን፣ የሚቀርቡት መባና መሥዋዕት የሚያመልከውን ሰው ኅሊና ፍጹም ሊያደርጉ አልቻሉም።

10 እነዚህ ሁሉ አዲሱ ሥርዐት እስኪመጣ ድረስ የሚደረጉ የምግብና የመጠጥ እንዲሁም የተለያዩ የመንጻት ሥርዐቶች ብቻ ናቸው።

11 ክርስቶስ አሁን ስላሉት መልካም ነገሮች ሊቀ ካህናት ሆኖ በመጣ ጊዜ በሰው እጅ ወዳልተሠራችው፣ ከዚህ ፍጥረት ወዳ ልሆነችው ታላቅና ፍጹም ድንኳን ገባ።

12 የገባውም የፍየልንና የጥጃዎችን ደም ይዞ አይደለም፤ ነገር ግን የዘላለም ቤዛነት ሊያስገኝ የራሱን ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገባ።