ዕብራውያን 13 NASV

የመጨረሻ ምክር

1 እርስ በርሳችሁ እንደ ወንድማማች ተዋደዱ።

2 እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ አንዳንዶች ይህን ሲያደርጉ፣ ሳያውቁ መላእክትን አስተናግደዋልና።

3 በእስር ላይ ያሉትን ከእነርሱ ጋር እንደታሰራችሁ ሆናችሁ ዐስቡአቸው፤ እንዲሁም በሰው እጅ የሚንገላቱትን ራሳችሁ መከራ እንደምትቀበሉ አድርጋችሁ ዐስቡአቸው።

4 ጋብቻ በሁሉም ዘንድ ይከበር፤ መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በአመንዝሮችና በሴሰኞች ሁሉ ላይ ይፈርዳል።

5 ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣“ከቶ አልተውህም፤በፍጹም አልጥልህም” ብሎአል።

6 ስለዚህ በሙሉ ልብ፣“ጌታ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም፤ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” እንላለን።

7 የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን መሪዎቻችሁን ዐስቡ፤ የኑሮአቸውን ፍሬ ተመልከቱ፤ በእምነታቸውም ምሰሉአቸው።

8 ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንት፣ ዛሬም ለዘላለምም ያው ነው።

9 በልዩ ልዩ ዐይነት እንግዳ ትምህርቶች አትወሰዱ፤ ልባችን የሚጸናው በጸጋ እንጂ የምግብ ሥርዐት በመጠበቅ አይደለም፤ ይህንን ሥርዐት የሚጠብቁት እንኳ በዚህ አልተጠቀሙም።

10 በድንኳኒቱም የሚያገለግሉ ከዚያ ሊበሉ መብት ያላገኙበት መሠዊያ አለን።

11 ሊቀ ካህናቱ ስለ ኀጢአት ስርየት የሚሆነውን የእንስሳት ደም ይዞ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባል፤ የእንስሳቱ ሥጋ ግን ከሰፈር ውጭ ይቃጠላል።

12 እንዲሁም ኢየሱስ በራሱ ደም አማካይነት ሕዝቡን ሊቀድስ ከከተማው በር ውጭ መከራን ተቀበለ።

13 ስለዚህ እኛም እርሱ የተሸከመውን ውርደት ተሸክመን ከሰፈር ውጭ ወደ እርሱ እንውጣ።

14 ምክንያቱም በዚህ ቋሚ ከተማ የለንም፤ ነገር ግን ወደ ፊት የምትመጣዋን ከተማ እንጠብቃለን።

15 ስለዚህ ዘወትር የምስጋናን መሥዋዕት ይኸውም ለስሙ የሚመስክሩ የከንፈሮችን ፍሬ በኢየሱስ አማካይነት ለእግዚአብሔር እናቅርብ።

16 ደግሞም መልካም ማድረግንና ያላችሁንም ከሌሎች ጋር መካፈልን አትርሱ፤ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘው እንደዚህ ባለው መሥዋዕት ነውና።

17 ለመሪዎቻችሁ ታዘዙ፤ ተገዙላቸውም። ምክንያቱም እነርሱ በብርቱ የሚያስጠይቃቸው ነገር ስላለባቸው፣ ስለ ነፍሳችሁ ጒዳይ ይተጋሉ። ስለዚህ ሥራቸውን በሐዘን ሳይሆን በደስታ ማከናወን እንዲችሉ ታዘዟቸው። አለበለዚያ አይበጃችሁም።

18 ለእኛ ደግሞ ጸልዩልን። በሁሉም መንገድ በመልካም አኗኗር ለመኖር የሚናፍቅ ንጹሕ ኅሊና እንዳለን ርግጠኞች ነን።

19 በተለይም ወደ እናንተ በፍጥነት ተመልሼ እንድመጣ ትጸልዩል ዘንድ ዐደራ እላችኋለሁ።

20 በዘላለም ኪዳን ደም የበጎች ታላቅ እረኛ የሆነውን ጌታችን ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው የሰላም አምላክ፣

21 ፈቃዱን እንድታደርጉ በመልካም ነገር ሁሉ ያስታጥቃችሁ፤ ደስ የሚያሰኘውንም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ያድርግ፤ ለእርሱ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።

22 ወንድሞች ሆይ፤ የጻፍሁላችሁ መልእክት አጭር እንደ መሆኑ፣ የምክር ቃሌን በትዕግሥት እንድትቀበሉ ዐደራ እላችኋለሁ።

23 ወንድማችን ጢሞቴዎስ እንደተፈታ ታውቁ ዘንድ እፈልጋለሁ፤ ቶሎ ከመጣ፣ ከእርሱ ጋር ላያችሁ እመጣለሁ።

24 ለመሪዎቻችሁ ሁሉና ለቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከኢጣሊያ የሆኑትም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።

25 ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13