1 ወንድሞቼ ሆይ፤ ክቡር በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የምታምኑ እንደመሆናችሁ አድልዎ አታድርጉ።
2 የወርቅ ቀለበት ያደረገና ያማረ ልብስ የለበሰ ሰው ወደ ጉባኤያችሁ ቢመጣ እንዲሁም ያደፈ ልብስ የለበሰ ድኻ ሰው ቢገባ፣
3 ያማረ ልብስ ለለበሰው የተለየ አክብሮት በማሳየት፣ “ለአንተ የሚሆን መልካም መቀመጫ ይኸውልህ” ብትሉትና ድኻውን ሰው ግን፣ “አንተ በዚያ ቁም” ወይም “ከእግሬ በታች በወለሉ ላይ ተቀመጥ” ብትሉት፣
4 በመካከላችሁ አድልዎ ማድረጋችሁ አይደለምን? ደግሞስ በክፉ ሐሳብ የተያዛችሁ ፈራጆች መሆናችሁ አይደለምን?
5 የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፤ ስሙ፤ እግዚአብሔር በእምነት ባለጠጋ እንዲሆኑና እርሱን ለሚወዱም ተስፋ የተሰጣቸውን መንግሥት እንዲወርሱ የዚህን ዓለም ድኾች አልመረጠምን?
6 እናንተ ግን ድኾችን አዋረዳችሁ፤ እናንተን የሚያስጨንቋችሁ ሀብታሞች አይደሉምን? ወደ ፍርድ ቤት የሚጐትቷችሁስ እነርሱ አይደሉምን?
7 በእናንተ የተጠራውን ክቡር የሆነውን ስም የሚሳደቡ እነርሱ አይደሉምን?