ያዕቆብ 3:4-10 NASV

4 ወይም መርከቦችን ተመልከቱ፤ ምንም እንኳ እጅግ ትልቅና በኀይለኛ ነፋስ የሚነዱ ቢሆኑም የመርከቡ ነጂ በትንሽ መሪ ወደሚፈልገው አቅጣጫ ይመራቸዋል።

5 እንዲሁም ምላስ ትንሽ የሰውነት ክፍል ሆና ሳለ በታላላቅ ነገሮች ትኵራራለች፤ ትልቅ ጫካ በትንሽ እሳት እንዴት ተቃጥሎ እንደሚጠፋ አስተውሉ፤

6 ምላስም እንደ እሳት ናት፤ በሰውነት ክፍሎቻችን መካከል የምትገኝ የክፋት ዓለም ናት፤ ሰውነትን ሁሉ ታረክሳለች፤ ደግሞም የፍጥረትን ሩጫ ታቃጥላለች፤ ራሷም በገሃነም ትቃጠላለች።

7 ማናቸውም ዐይነት እንስሳ፣ አዕዋፍ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡና፣ በባሕር ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት ሁሉ መገራት ችለዋል፤ በሰውም ተገርተዋል።

8 ነገር ግን ምላስን መግራት የሚችል ማንም ሰው የለም፤ የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት።

9 በምላሳችን ጌታንና አብን እንባርካለን፤ በእርሷም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን።

10 ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ፤ ወንድሞቼ ሆይ፤ ይህ ሊሆን አይገባም።