ይሁዳ 1:1-6 NASV

1 የኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይና የያዕቆብ ወንድም ይሁዳ፤ለተጠሩት፣ በእግዚአብሔር አብ ለተወደዱትና በኢየሱስ ክርስቶስ ለተጠበቁት፤

2 ምሕረት፣ ሰላምና ፍቅር ይብዛላችሁ።

3 ወዳጆች ሆይ፤ አብረን ስለምንካፈለው ድነት ልጽፍላችሁ እጅግ ጓጒቼ ነበር፤ ነገር ግን ለቅዱሳን አንዴና ለመጨረሻ ስለ ተሰጠው እምነት እንድትጋደሉ ለመምከር እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።

4 ከረጅም ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንድ ሰዎች ሾልከው ወደ እናንተ ገብተዋልና፤ እነርሱ ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌላቸው፣ የአምላካችንን ጸጋ በርኵሰት የሚለውጡና እርሱ ብቻ ልዑል ገዣችንና ጌታችን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው።

5 ምንም እንኳ አስቀድማችሁ ይህን ሁሉ የምታውቁ ቢሆንም፣ ጌታ ሕዝቡን ከግብፅ ምድር እንዴት እንዳወጣ፣ በኋላ ግን ያላመኑትን እንዳጠፋ ላስታውሳችሁ እወዳለሁ።

6 የሥልጣን ስፍራቸውን ያልጠበቁትን ነገር ግን መኖሪያቸውን የተዉትን መላእክት በዘላለም እስራት እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ በጨለማ ጠብቆአቸዋል።