32 ከዚያም ዮሐንስ እንዲህ ሲል ምስክርነቱን ሰጠ፤ “መንፈስ እንደ ርግብ ከሰማይ ወርዶ በእርሱ ላይ ሲያርፍ አየሁ፤
33 በውሃ እንዳጠምቅ የላከኝም፣ ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚያጠምቀው፣ መንፈስ ሲወርድና በርሱ ላይ ሲያርፍ የምታየው እርሱ ነው’ ብሎ እስከ ነገረኝ ድረስ እኔም አላወቅሁትም ነበር፤
34 አይቻለሁ፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ እመሰክራለሁ።”
35 በማግሥቱ፣ ዮሐንስ ከሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደ ገና እዚያው ቦታ ነበር፤
36 ኢየሱስንም በዚያ ሲያልፍ አይቶ፣ “እነሆ! የእግዚአብሔር በግ” አለ።
37 ሁለቱ ደቀ መዛሙርትም ይህን ሲናገር ሰምተው ኢየሱስን ተከተሉት።
38 ኢየሱስም ዘወር ብሎ ሲከተሉት አየና፣ “ምን ትፈልጋላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው።እነርሱም፣ “ረቢ፣ የት ትኖራለህ?” አሉት፤ ‘ረቢ’ ማለት መምህር ማለት ነው።