ዮሐንስ 16:17-23 NASV

17 ከደቀ መዛሙርቱም አንዳንዶቹ፣ “ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ እንዲሁም፣ ‘ወደ አብ ስለምሄድ’ ሲል ምን ማለቱ ነው?” ተባባሉ፤

18 “‘ጥቂት ጊዜ’ ማለቱስ ምን ይሆን? የሚለውም ነገር አልገባንም” እያሉ ይጠያየቁ ነበር።

19 ኢየሱስም ሊጠይቁት እንደ ፈለጉ ባወቀ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ፣ ‘ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ’ ስላልኋችሁ፣ ምን ማለቴ እንደሆነ እርስ በርሳችሁ ትጠያየቃላችሁ?

20 እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ ታለቅሳላችሁ፤ ታዝናላችሁም፤ ዓለም ግን ሐሤት ያደርጋል፤ ይሁን እንጂ ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።

21 ሴት ቀኗ ደርሶ ስትወልድ ትጨነቃለች፤ ከተገላገለች በኋላ ግን፣ ሰው ወደ ዓለም ስለ መጣ ጭንቋን ትረሳለች፤

22 ለእናንተም እንደዚሁ አሁን የሐዘን ጊዜ ነው፤ ሆኖም እንደ ገና ስለማያችሁ ደስ ይላችኋል፤ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም።

23 በዚያ ቀን ከእኔ ምንም አትለምኑም፤ እውነት እላችኋለሁ፤ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል።