21 ኢየሱስም እንዲህ አላት፤ “አንቺ ሴት፤ በዚህ ተራራም ሆነ በኢየሩሳሌም ለአብ የማትሰግዱበት ጊዜ እንደሚመጣ እመኚኝ።
22 እናንተ ሳምራውያን ለማታውቁት ትሰግዳላችሁ፤ እኛ ግን ድነት ከአይሁድ ስለ ሆነ ለምናውቀው እንሰግዳለን።
23 በእውነት የሚሰግዱ ለአብ በመንፈስና በእውነት የሚሰግዱበት ጊዜ ይመጣል፤ አሁንም መጥቶአል፤ አብም እንደዚህ በእውነት የሚሰግዱለትን ይፈልጋል።
24 እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊሰግዱለት ይገባል።”
25 ሴትዮዋም፣ “ክርስቶስ የተባለ መሲሕ እንደሚመጣ ዐውቃለሁ፤ እርሱ ሲመጣ ሁሉን ነገር ይነግረናል” አለችው።
26 ኢየሱስም፣ “የማነጋግርሽ እኮ እኔ እርሱ ነኝ” ሲል ገልጦ ነገራት።
27 በዚህ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ተመልሰው መጡ፤ ከሴት ጋር ሲነጋገር በማግኘታቸው ተደነቁ፤ ሆኖም ግን፤ “ምን ፈለግህ?” ወይም፣ “ከእርሷ ጋር የምትነጋገረው ለምንድን ነው?” ብሎ የጠየቀው ማንም አልነበረም።