ገላትያ 1 NASV

1 ከሰዎች ወይም በሰው ከተላከው ሳይሆን፣ በኢየሱስ ክርስቶስና ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ ከሆነው ከጳውሎስ፤

2 አብረውኝም ካሉት ወንድሞች ሁሉ፤

በገላትያ ላሉት አብያተ ክርስቲያናት

3 ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።

4 እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ፣ ከዚህ ክፉ ዓለም ያድነን ዘንድ ስለ ኀጢአታችን ራሱን ሰጠ፤

5 ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ክብር ይሁን፤ አሜን።

ወንጌል አንዲት ናት

6 በክርስቶስ ጸጋ የጠራችሁን እርሱን ትታችሁ፣ ወደ ተለየ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ መዞራችሁ ደንቆኛል፤

7 እንደ እውነቱ ከሆነ ሌላ ወንጌል የለም። የሚያደነጋግሯችሁና የክርስቶስን ወንጌል ለማጣመም ጥረት የሚያደርጉ አንዳንድ ሰዎች አሉ።

8 ነገር ግን እኛም ብንሆን ወይም የሰማይ መልአክ፣ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ እርሱ ለዘላለም የተረገመ ይሁን።

9 ቀደም ብለን እንዳልነው፣ አሁንም ደግሜ እላለሁ፤ ማንም ከተቀበላችሁት ሌላ የተለየ ወንጌል ቢሰብክላችሁ፣ እርሱ ለዘላለም የተረገመ ይሁን።

10 አሁን እኔ ጐሽ ለመባል የምሻው በሰዎች ዘንድ ነው ወይስ በእግዚአብሔር ዘንድ? ወይስ ሰዎችን ደስ ለማሰኘት እየተጣጣርሁ ነው? ሰዎችን ደስ ለማሰኘት የምጥር ብሆን ኖሮ፣ የክርስቶስ አገልጋይ ባልሆንሁ ነበር።

ጳውሎስ በእግዚአብሔር መጠራቱ

11 ወንድሞች ሆይ፤ የሰበክሁላችሁ ወንጌል ሰው ሠራሽ አለመሆኑን እንድታውቁ እፈልጋለሁ፤

12 ከማንም ሰው አልተቀበልሁትም፤ ከማንም አልተማርሁትም፤ ይልቁንስ በመገለጥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ተቀበልሁት።

13 ቀድሞ በአይሁድ ሃይማኖት እንዴት እንደኖርሁ፣ የእግዚአብሔርንም ቤተ ክርስቲያን እንዴት በእጅጉ እንዳሳደድሁ፣ ለማጥፋትም እንዴት እንደጣርሁ ሰምታችኋል፤

14 በእኔ ዕድሜ ዘመን ከነበሩት ከብዙዎቹ አይሁድ ይበልጥ በአይሁድ ሃይማኖት እልቅ ነበር፤ ስለ አባቶቼም ወግ እጅግ ቀናተኛ ነበርሁ።

15 ነገር ግን፣ ከእናቴ ማሕፀን ጀምሮ የለየኝና በጸጋው የጠራኝ እግዚአብሔር፣

16 በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ እንድሰብክ ልጁን በእኔ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፣ ከማንም ሥጋ ለባሽ ጋር አልተማከርሁም፤

17 ከእኔ በፊት ሐዋርያት ወደ ሆኑትም ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፤ ነገር ግን ወዲያው ወደ ዐረብ አገር ሄድሁ፤ በኋላም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ።

18 ከዚያም ከሦስት ዓመት በኋላ፣ ጴጥሮስን አገኘው ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣሁ፤ ከእርሱም ጋር ዐሥራ አምስት ቀን ተቀመጥሁ።

19 ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር፣ ከሐዋርያት ማንንም አላየሁም።

20 በምጽፍላችሁ ነገር በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት እንደማልናገር አስረግጬ እነግራችኋለሁ።

21 ከዚያም በኋላ፣ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር ሄድሁ።

22 በክርስቶስ ያሉት የይሁዳ አብያተ ክርስቲያናትም ፊቴን አይተው አያውቁም ነበር፤

23 እነርሱ ግን፣ “ቀድሞ እኛን ሲያሳድድ የነበረ ሰው፣ ከዚህ በፊት ሊያጠፋው ይፈልግ የነበረውን እምነት አሁን እየሰበከ ነው” የሚለውን ወሬ ብቻ ሰምተው ነበር፤

24 በእኔም ምክንያት እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6