ገላትያ 3:10-16 NASV

10 ሕግን በመጠበቅ የሚተማመኑ ሁሉ ከርግማን በታች ናቸው፤ “በሕግ መጻሕፍት የተጻፈውን ሁሉ የማያደርግ የተረገመ ነው” ተብሎ ተጽፎአልና።

11 “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ስለ ተባለ፣ ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንደማይጸድቅ ግልጽ ነው።

12 ሕግ በእምነት ላይ የተመሠረተ አይደለም፤ ነገር ግን “ሕግጋትን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ በሕይወት ይኖራል” ተብሎአል።

13 “በዕንጨት ላይ የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ስለ ተጻፈ፣ ክርስቶስ ስለ እኛ ርግማን ሆኖ ከሕግ ርግማን ዋጅቶናል፤

14 ለአብርሃም የተሰጠው በረከት፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ለአሕዛብ እንዲደርስ ዋጅቶናል፤ ይኸውም በእምነት የመንፈስን ተስፋ እንድንቀበል ነው።

15 ወንድሞች ሆይ፤ ከሰው ዕለታዊ ሕይወት የተለመደውን ምሳሌ አድርጌ ላቅርብ፤ የሰው ኪዳን እንኳ አንድ ጊዜ ከጸደቀ በኋላ ማንም ሊሽረው ወይም በእርሱ ላይ ሊጨምርበት እንደማይችል ሁሉ፣ በዚህም ጒዳይ ቢሆን እንደዚሁ ነው።

16 የተስፋውም ቃል የተነገረው ለአብርሃምና ለዘሩ ነበር፤ መጽሐፍ፣ ለብዙ ሰዎች እንደሚነገር፣ “ለዘሮቹ” አይልም፤ ነገር ግን ለአንድ ሰው እንደሚነገር፣ “ለዘርህ” ይላል፤ እርሱም ክርስቶስ ነው።