3 ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያነጻ ሰው ይቀመጣል፤ ሌዋውያንንም አንጽቶ እንደ ወርቅና እንደ ብር ያጠራቸዋል፤ ከዚያም እግዚአብሔር ቊርባንን በጽድቅ የሚያቀርቡ ሰዎች ይኖሩታል፤
4 በዚያ ጊዜ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ቊርባን እንዳለፉት ቀናትና እንደ ቀድሞው ዘመን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል።
5 “ስለዚህ እኔ ለፍርድ ወደ እናንተ እመጣለሁ፤ በመተተኞች፣ በአመንዝራዎች፣ በሐሰት በሚምሉ፣ የሠራተኞችን ደመወዝ በሚከለክሉ፣ መበለቶችንና ድኻ አደጉን በሚጨቍኑ፣ መጻተኞችን ፍትሕ በሚነፍጉ፣ እኔንም በማይፈሩት ላይ እመሰክርባቸው ዘንድ እፈጥናለሁ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።
6 “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም፤ ስለዚህ እናንተ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ አልጠፋችሁም።
7 ከአባቶቻችሁ ዘመን ጀምሮ ከትእዛዛቴ ፈቀቅ ብላችኋል፤ አልጠበቃችኋቸውምም፤ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።“እናንተ ግን፣ የምንመለሰው እንዴት ነው ትላላችሁ?”
8 “ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን?” እናንተ ግን ትሰርቁኛላችሁ።“እናንተ ግን፣ ‘እንዴት እንሰርቅሃለን?’ ትላላችሁ።“ዐሥራትና መባ ትሰርቁኛላችሁ፤
9 እናንተም፣ መላው ሕዝባችሁም ስለምትሰርቁኝ የተረገማችሁ ናችሁ።