1 እግዚአብሔር የጽዮንን ሴት ልጅ፣በቍጣው ደመና እንዴት ጋረዳት!ከሰማይ ወደ ምድር፣የእስራኤልን ክብር ወርውሮ ጣለው፤በቍጣው ቀን፣የእግሩን መቀመጫ አላስታወሰም።
2 የያዕቆብን መኖሪያ ሁሉ፣እግዚአብሔር ያለ ርኅራኄ ዋጣቸው፤የይሁዳን ሴት ልጅ ምሽጎች፣በቍጣው አፈረሳቸው፤መንግሥቷንና መሳፍንቷን፣በማዋረድ ወደ ምድር ጣላቸው።
3 በጽኑ ቍጣው፣የእስራኤልን ቀንድ ሁሉ ሰበረ፤ጠላት በተቃረበ ጊዜ፣ቀኝ እጁን ወደ ኋላ መለሰ፤በዙሪያው ያለውን ሁሉ እንደሚበላ እሳት፣በያዕቆብ ላይ የእሳት ነበልባል ነደደ።
4 እንደ ጠላት ቀስቱን ገተረ፤ቀኝ እጁ ተዘጋጅታለች፤ለዐይን ደስ የሚያሰኙትን ሁሉ፤እንደ ጠላት ዐረዳቸው፤በጽዮን ሴት ልጅ ድንኳን ላይ፣ቍጣውን እንደ እሳት አፈሰሰ።