1 ሳሙኤል 30:11-17 NASV

11 እነርሱም በምድረ በዳ አንድ ግብፃዊ አገኙ፤ ወደ ዳዊትም አመጡት፤ የሚጠጣውን ውሃና የሚበላውን ምግብ ሰጡት።

12 እንደዚሁም የበለስ ጥፍጥፍ ቍራሽና ሁለት ደረቅ የወይን ዘለላዎች ሰጡት። ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ምንም እህል ስላልበላ፣ ውሃም ስላልጠጣ ይህን ከበላ በኋላ ነፍሱ ተመለሰች።

13 ዳዊትም፣ “አንተ የማን ነህ? የመጣኸውስ ከየት ነው?” ብሎ ጠየቀው።እርሱም እንዲህ አለው፤ “እኔ ግብፃዊ ስሆን፣ የአንድ አማሌቃዊ ባሪያ ነኝ፤ ከሦስት ቀን በፊት ታምሜ በነበረበት ጊዜ ጌታዬ ጥሎኝ ሄደ።

14 የከሊታውያንን ደቡብ፣ የይሁዳን ግዛትና የካሌብን ደቡብ ወረርን፤ ጺቅላግንም በእሳት አጋየናት።”

15 ዳዊትም፣ “ታዲያ ወራሪው ሰራዊት ወዳለበት መርተህ ታደርሰኛለህ?” ሲል ጠየቀው።እርሱም፣ “እንደማትገድለኝ ወይም ለጌታዬ አሳልፈህ እንደማትሰጠኝ በእግዚአብሔር ማልልኝ እንጂ እነዚህ ወራሪዎች ወዳሉበት አደርስሃለሁ” አለው።

16 ዳዊትን ወደ ታች መርቶ ባደረሰው ጊዜም፣ ወራሪዎቹ ከፍልስጥኤማውያንና ከይሁዳ ምድር ከወሰዱት ታላቅ ምርኮ የተነሣ በየቦታው ተበታትነው ይበሉ፣ ይጠጡና ይዘፍኑ፣ ይጨፍሩም ነበር።

17 ዳዊት፣ ከዚያች ዕለት ማታ ጀምሮ እስከ ማግሥቱ ምሽት ድረስ ወጋቸው፤ በግመል ተቀምጠው ከሸሹት አራት መቶ ወጣቶች በስተቀር፣ ከመካከላቸው ያመለጠ አንድም አልነበረም።