9 ወደ ኪዶን ዐውድማ በደረሱ ጊዜ በሬዎቹ አደናቅፏቸው ስለ ነበር፣ ዖዛ ታቦቱን ለመደገፍ እጁን ዘረጋ።
10 ታቦቱን በእጁ ስለ ነካ፣ የእግዚአብሔር ቍጣ በዖዛ ላይ ነደደ፤ ስለዚህም በዚያው በእግዚአብሔር ፊት ሞተ።
11 የእግዚአብሔር ቍጣ ዖዛን በድንገት ስለ ቀሠፈው ዳዊት አዘነ፤ ያም ቦታ እስከ ዛሬ ድረስ የዖዛ ስብራት ተብሎ ይጠራል።
12 ዳዊት በዚያን ዕለት እግዚአብሔርን ስለ ፈራ፣ “ታዲያ የእግዚአብሔርን ታቦት ወደ እኔ እንዴት ማምጣት እችላለሁ?” አለ።
13 ስለዚህ ታቦቱን ወደ ዳዊት ከተማ በመውሰድ ፈንታ የጋት ሰው ወደ ሆነው ወደ አቢዳራ ቤት ወሰደው።
14 የእግዚአብሔርም ታቦት በአቢዳራ ቤት ከቤተ ሰቡ ጋር ሦስት ወር ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርም ቤተ ሰቡንና ያለውንም ሁሉ ባረከ።