1 ዳዊት ከሰራዊቱ አለቆች ጋር ሆኖ በመሰንቆ፣ በበገናና በጸናጽል ድምፅ እየታጀቡ ትንቢት የሚናገሩትን ከአሳፍ፣ ከኤማንና ከኤዶታም ቤተ ሰብ መካከል መርጦ መደበ፤ ይህን አገልግሎት የሚያከናውኑትም ሰዎች ዝርዝር እንደሚከተለው ነው፤
2 ከአሳፍ ወንዶች ልጆች፤ዘኩር፣ ዮሴፍ፣ ነታንያ፣ አሼርኤላ። የአሳፍ ልጆች በአሳፍ አመራር ሥር ነበሩ፤ አሳፍም በንጉሡ አመራር ሥር ነበረ።
3 ከኤዶታም ወንዶች ልጆች፤ጎዶልያስ፣ ጽሪ፣ የሻያ፣ ሰሜኢ፣ ሐሸብያ፣ መቲትያ። እነዚህ ስድስቱ በመሰንቆ እግዚአብሔርን እያመሰገነና እየወደሰ ትንቢት በተናገረው አባታቸው በኤዶታም አመራር ሥር ነበሩ።
4 ከኤማን ወንዶች ልጆች፤ቡቅያ፣ መታንያ፣ ዓዛርዔል፣ ሱባኤል፣ ኢያሪሙት፣ ሐናንያ፣ ሐናኒ፣ ኤልያታ፣ ጊዶልቲ፣ ሮማንቲዔዘር፣ ዮሽብቃሻ፣ መሎቲ፣ ሆቲር፣ መሐዝዮት።
5 እነዚህም ሁሉ የንጉሡ ባለ ራእይ የኤማን ልጆች ነበሩ። እርሱን ከፍ ከፍ እንዲያደርጉትም እግዚአብሔር በገባለት ቃል መሠረት ሰጡት። እግዚአብሔር ለኤማን ዐሥራ አራት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ሰጠው።
6 እነዚህ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በጸናጽል፣ በመሰንቆና በበገና ድምፅ ለሚቀርበው የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት በአባቶቻቸው አመራር ሥር ነበሩ። አሳፍ፣ ኤዶታምና ኤማን ደግሞ በንጉሡ የበላይ አመራር ሥር ነበሩ።
7 እነዚህም ከቤተ ዘመዶቻቸው ጋር በመሆን ሁሉም ወደ እግዚአብሔር በሚቀርበው ዜማ የሠለጠኑና የተካኑ ነበሩ፤ ቊጥራቸውም ሁለት መቶ ሰማንያ ስምንት ነበረ።