1 ዜና መዋዕል 5 NASV

ሮቤል

1 የእስራኤል የበኵር ልጅ የሮቤል ልጆች፤ ሮቤል የበኵር ልጅ ቢሆንም፣ የአባቱን መኝታ ስላረከሰ፣ የብኵርና መብቱ ለእስራኤል ልጅ ለዮሴፍ ልጆች ተሰጥቶአል። ከዚህም የተነሣ ትውልዱ የበኵርነቱን ተራ ይዞ ሊቈጠር አልቻለም።

2 ይሁዳ ከወንድሞቹ ይልቅ ብርቱ ነበረ፤ ገዥ የወጣው ከእርሱ ቢሆንም፣ የብኵርና መብቱ የተላለፈው ለዮሴፍ ነበረ።

3 የእስራኤል የበኵር ልጅ የሮቤል ወንዶች ልጆች፤ሄኖኅ፣ ፋሉሶ፣ አስሮን፣ ከርሚ።

4 የኢዩኤል ዘሮችልጁ ሸማያ፣ ልጁ ጎግ፣ ልጁሰሜኢ፣

5 ልጁ ሚካ፣ልጁ ራያ፣ ልጁ ቢኤል፣

6 የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር ማርኮ የወሰደው ልጁ ብኤራ።

7 የቤተ ሰቡ የዘር ትውልድ በየጐሣ በየጐሣው ሲቈጠር እንደሚከተለው ነው፤የጐሣ አለቃ የሆነው ኢዮኤል፣ ዘካርያስ፣

8 የኢዮኤል ልጅ፣ የሽማዕ ልጅ፣ የዖዛዝ ልጅ ቤላ፣ እነዚህ ከአሮዔር እስከ ናባውና እስከ በኣልሜዎን ድረስ በሚገኘው ምድር ላይ ሰፈሩ።

9 ከብቶቻቸው በገለዓድ ምድር በዝተው ስለ ነበር በምሥራቅ በኩል ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ እስከ ምድረ በዳው ዳርቻ ድረስ የሚገኘውን ምድር ያዙ።

10 በሳኦልም ዘመነ መንግሥት በእጃቸው ተመትተው ድል ከተደረጉት አጋራውያን ጋር ተዋጉ፤ በመላው የገለዓድ ምሥራቃዊ ክፍል የሚገኙትን መኖሪያዎቻቸውን ያዙ።

ጋድ

11 የጋድ ነገድ ደግሞ ከእነርሱ ቀጥሎ እስከ ሰልካ ድረስ በሚገኘው በባሳን ምድር ኖሩ፤

12 አለቃው ኢዮኤል፣ ሁለተኛው ሳፋም ከዚያም ያናይና ሰፋጥ ሆነው በባሳን ተቀመጡ።

13 ቤተ ዘመዶቻቸውም በየቤተ ሰቡ እነዚህ ነበሩ፤ ሚካኤል፣ ሜሱላም፣ ሳባ፣ ዮራይ፣ ያካን፣ ዙኤ፣ ኦቤድ፤ ባጠቃላይ ሰባት ነበሩ።

14 እነዚህ ደግሞ የቡዝ ልጅ፣ የዬዳይ ልጅ፣ የኢዬሳይ ልጅ፣ የሚካኤል ልጅ፣ የገለዓድ ልጅ፣ የኢዳይ ልጅ፣ የዑሪ ልጅ፣ የሑሪ ልጅ፣ የአቢካኢል ልጆች ናቸው።

15 የቤተ ሰባቸውም አለቃ የጉኒ ልጅ፣ የአብዲኤል ልጅ አሒ ነበረ።

16 ጋዳውያንም በገለዓድ፣ በባሳንና እስከ ዳርቻዋ በሚገኙት መንደሮች እንዲሁም በሳሮን በሚገኙ የግጦሽ ስፍራዎች ሁሉና ከዚያም ወዲያ አልፈው ተቀመጡ።

17 እነዚህ ሁሉ በትውልድ መዝገብ የሰፈሩት በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአታምና በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት ነው።

18 የሮቤል፣ የጋድና የምናሴ ነገድ እኩሌታ አርባ አራት ሺህ ሰባት መቶ ሥልሳ ብቁ የጦር ሰዎች ነበሩአቸው። እነርሱም ጋሻ መያዝ፣ ሰይፍ መምዘዝና ቀስት መሳብ የሚችሉ ጠንካራና በውጊያ የሠለጠኑ ናቸው።

19 እነዚህም በአጋራውያን፣ በኢጡር፣ በናፌስ፣ በናዳብ ላይ ዘመቱ።

20 በጦርነቱም ላይ ወደ እግዚአብሔር ጮኸው ስለ ነበር፣ በውጊያው ረዳቸው፤ አጋራውያንንና የጦር አጋሮቻቸውን ሁሉ አሳልፎ ሰጣቸው፤ ስለ ታመኑበትም ጸሎታቸውን ሰማ።

21 የአጋራውያንንም እንስሶች ማረኩ፤ እነዚህም አምሳ ሺህ ግመሎች፣ ሁለት መቶ አምሳ ሺህ በጎችና ሁለት ሺህ አህዮች ነበሩ። እንዲሁም አንድ መቶ ሺህ ሰው ማረኩ።

22 ውጊያው የእግዚአብሔር ስለ ነበር ሌሎችም ብዙ ሰዎች ተገደሉ። እስከ ምርኮ ጊዜ ድረስ ምድሪቱ በእጃቸው ነበረች።

እኩሌታው የምናሴ ነገድ

23 የምናሴ ነገድ እኩሌታ ሕዝብ ቍጥር ብዙ ነበረ፤ እነርሱም ከባሳን ጀምሮ እስከ በኣልአርሞንዔም ድረስ ባለው ምድር ሰፈሩ፤ ይህም እስከ ሳኔር አርሞንዔም ተራራ ድረስ ማለት ነው።

24 የየቤተ ሰቡም አለቆች እነዚህ ነበሩ፤ ዔፌር፤ ይሽዒ፣ ኤሊኤል፣ ዓዝርኤል፣ ኤርምያ፣ ሆዳይዋ፣ ኢየድኤ፤ እነዚህ ጀግና ተዋጊዎች፣ የታወቁ ሰዎችና የየቤተ ሰባቸው አለቆች ነበሩ።

25 ይሁን እንጂ ለአባቶቻቸው አምላክ ታማኞች አልሆኑም፤ እግዚአብሔር ከፊታቸው ያጠፋቸውን የምድሪቱን አሕዛብ አማልክት በማምለክ አመነዘሩ።

26 ስለዚህ የእስራኤል አምላክ የአሦርን ንጉሥ የፎሐን መንፈስ ይኸውም የቴልጌልቴልፌልሶርን መንፈስ አነሣሥቶ የሮቤልን፣ የጋድንና፣ የምናሴን ነገድ እኩሌታ ማርኮ እንዲወስድ አደረገ። እነዚህንም ወደ አላሔ፣ ወደ አቦር፣ ወደ ሃራና ወደ ጎዛን ወንዝ ዳርቻ አፈለሳቸው፤ እነርሱም እስከ ዛሬ ድረስ በዚያ ይገኛሉ።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29