10 ኢዮአብም ከፊቱና ከኋላው ጦር መኖሩን አየ፤ ስለዚህ በእስራኤል የታወቁትን ጀግኖች መርጦ ሶርያውያንን እንዲገጥሙ አሰለፋቸው።
11 የቀሩትም ሰዎች በወንድሙ በአቢሳ ሥር ሆነው አሞናውያንን እንዲገጥሙ አሰለፋቸው።
12 ኢዮአብም እንዲህ አለ፤ “ሶርያውያን ከበረቱብኝ አንተ ትረዳኛለህ፤ አሞናውያን ከበረቱብህ ደግሞ እኔ እረዳሃለሁ።
13 እንግዲህ በርቱ፤ ስለ ሕዝባችንና ስለ አምላካችን ከተሞች ብለን በጀግንነት እንዋጋ፤ እግዚአብሔርም ደስ ያሰኘውን ያድርግ።”
14 ከዚያም ኢዮአብና አብረውት ያሉት ወታደሮች ሶርያውያንን ለመውጋት ወደ ፊት ገሠገሡ፤ ሶርያውያንም ከፊታቸው ሸሹ።
15 አሞናውያንም ሶርያውያን መሸሻቸውን ሲያዩ፣ እነርሱም ከወንድሙ ከአቢሳ ፊት ሸሽተው ወደ ከተማዪቱ ገቡ፤ ስለዚህ ኢዮአብ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
16 ሶርያውያን በእስራኤል መሸነፋቸውን ሲያዩ፣ መልክተኞችን ልከው ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ ያሉትን ሶርያውያን አስመጡ፤ እነዚህንም የሚመራቸው የአድርአዛር ሰራዊት አዛዥ ሾፋክ ነበረ።