2 ዳዊትም ኢዮአብንና የሰራዊቱን አዛዦች፣ “ሄዳችሁ ከቤርሳቤህ እስከ ዳን ያሉትን እስራኤላውያን ቍጠሩ፤ ከዚያም ምን ያህል እንደሆኑ አውቅ ዘንድ ንገሩኝ” አላቸው።
3 ኢዮአብ ግን፣ “እግዚአብሔር የእስራኤልን ሰራዊት አሁን ካለው በላይ በመቶ እጥፍ ያብዛው፤ ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፤ ሁሉስ ቢሆኑ የጌታዬ ተገዢዎች አይደሉምን? ታዲያ ጌታዬ ይህን ማድረግ ለምን አስፈለገው? ለምንስ በእስራኤል ላይ በደል ያመጣል?” አለ።
4 ይሁን እንጂ የንጉሡ ቃል ኢዮአብን አሸነፈው፤ ስለዚህ ኢዮአብ ወጣ፤ በመላው እስራኤል ከተዘዋወረ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
5 ኢዮአብም የተዋጊዎቹን ሰዎች ቍጥር ለዳዊት አቀረበ፤ እነዚህም በመላው እስራኤል አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ ሺህ፣ በይሁዳ ደግሞ አራት መቶ ሰባ ሺህ ሲሆኑ፣ ሁሉም ሰይፍ መምዘዝ የሚችሉ ነበሩ።
6 ኢዮአብ ግን የንጉሡ ትእዛዝ አስጸያፊ ነበረና፣ የሌዊንና የብንያምን ነገድ ጨምሮ አልቈጠረም።
7 ይህ ትእዛዝ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እስራኤልን ቀጣ።
8 ከዚያም ዳዊት እግዚአብሔርን፣ “ይህን በማድረጌ እጅግ በድያለሁ፤ የፈጸምሁትም የስንፍና ሥራ ስለ ሆነ፣ የባሪያህን በደል እንድታስወግድ እለምንሃለሁ” አለ።