25 ዮሐንስ ተልእኮውን በማጠናቀቅ ላይ ሳለ፣ ‘እኔ ማን መሰልኋችሁ? እኔ እኮ እርሱ አይደለሁም፤ ነገር ግን የእግሩን ጫማ እንኳ መፍታት የማይገባ ከእኔ በኋላ ይመጣል’ ይል ነበር።
26 “እናንት ከአብርሃም ዘር የተወለዳችሁ ወንድሞች፤ ደግሞም በመካከላችሁ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ፤ ይህ የድነት መልእክት የተላከው ለሁላችንም ነው።
27 የኢየሩሳሌም ሰዎችና አለቆቻቸው ኢየሱስን አላወቁትም፤ ይሁን እንጂ በየሰንበቱ የሚነበበው የነቢያት ቃል እንዲፈጸም በእርሱ ፈረዱበት።
28 ለሞት የሚያበቃው አንድም ምክንያት ባያገኙበትም እንኳ ጲላጦስ የሞት ፍርድ እንዲፈርድበት ተማጸኑት።
29 ስለ እርሱ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ ከተሰቀለበት ዕንጨት አውርደው በመቃብር ውስጥ አስገቡት።
30 እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው።
31 ከገሊላ ጀምሮ እስከ ኢየሩሳሌም ከእነርሱ ጋር ለነበሩትም ብዙ ቀን ታያቸው፤ እነርሱም አሁን ለሕዝቡ ምስክሮቹ ናቸው።