1 ከአምስት ቀን በኋላ፣ ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከአንዳንድ ሽማግሌዎችና ጠርጡለስ ከሚባል ጠበቃ ጋር ወደ ቂሳርያ ወረደ፤ በጳውሎስም ላይ ያላቸውን ክስ ለአገረ ገዡ አቀረቡ።
2 ጳውሎስ ተጠርቶ በቀረበ ጊዜ፣ ጠርጠሉስ እንዲህ ሲል ክሱን አቀረበ፤ “ክቡር ፊልክስ ሆይ፤ በአንተ ዘመን ሰላም ለብዙ ጊዜ ሰፍኖልናል፤ አርቆ አስተዋይነትህም ለዚህ ሕዝብ መሻሻልን አስገኝቶለታል፤
3 በየቦታውና በየጊዜው ይህን ውለታ በታላቅ ምስጋና እንቀበላለን።
4 ነገር ግን ይበልጥ እንዳላደክምህ፣ በአጭሩ እንድ ትሰማን መልካም ፈቃድህን እለምንሃለሁ።
5 “ይህ ሰው፣ በዓለም ባሉት አይሁድ ሁሉ መካከል በሽታ ሆኖ ሁከት የሚያስነሣ፣ ደግሞም የናዝራውያን ወገን ቀንደኛ መሪ ሆኖ አግኝተነዋል።
6 ከዚህም በላይ ቤተ መቅደሱን ለማርከስ ሲሞክር አግኝተን ያዝነው። በሕጋችንም መሠረት ልንፈርድበት አስበን ነበር፤
7 ነገር ግን የጦር አዛዡ ሉስዮስ መጥቶ በታላቅ ኀይል ከእጃችን ነጥቆ ወሰደው፤ ከሳሾቹም ወደ አንተ እንዲመጡ አዘዘ።
8 እንግዲህ አንተ ራስህ መርምረኸው እርሱን የከሰስንበትን ነገር ሁሉ እውነት መሆኑን ልታረጋግጥ ትችላለህ።”
9 አይሁድም ነገሩን እንደ ተባለው መሆኑን በመደገፍ በክሱ ተባበሩ።
10 አገረ ገዡም እንዲናገር በእጁ ምልክት በሰጠው ጊዜ፣ ጳውሎስ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከብዙ ዘመን ጀምሮ የዚህ ሕዝብ ፈራጅ መሆንህን ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ የመከላከያ መልሴን የማቀርበው በደስታ ነው።
11 ልሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም የመጣሁት ከዐሥራ ሁለት ቀን በፊት መሆኑን አንተው ራስህ በቀላሉ ማረጋገጥ ትችላለህ።
12 ከሳሾቼም በቤተ መቅደስ ከማንም ጋር ስከራ ከር ወይም በምኵራብ ወይም በከተማ ውስጥ በየትኛውም ስፍራ ሕዝብን ሳነሣሣ አላገኙኝም።
13 አሁንም ለተከሰስሁበት ነገር ማስረጃ ሊያቀርቡልህ አይችሉም።
14 ይሁን እንጂ፣ እነርሱ ኑፋቄ በሚሉት በጌታ መንገድ የአባቶቻችንን አምላክ አመልካለሁ፤ በሕጉ የታዘዘውንና በነቢያት የተጻፈውን ሁሉ አምናለሁ፤
15 ደግሞም እንደነዚህ ሰዎች ሁሉ፣ ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን እንደሚነሡ በእግዚአብሔር ተስፋ አለኝ።
16 ስለዚህ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ንጹሕ ኅሊና እንዲኖረኝ ሁል ጊዜ እጥራለሁ።
17 “ከብዙ ዓመት በኋላም፣ ለድኻው ወገኔ ምጽዋትና መባ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም መጣሁ።
18 እነርሱም በቤተ መቅደስ የመንጻት ሥርዐት ፈጽሜ ይህንኑ ሳደርግ አገኙኝ፤ የሕዝብ ሁካታ ወይም ረብሻ አልነበረም።
19 ነገር ግን ክስ ካላቸው አንተ ፊት ቀርበው ሊከሱ የሚገባቸው ከእስያ አውራጃ የመጡ አንዳንድ አይሁድ አሉ፤
20 ወይም በዚህ ያሉት እነዚህ በሸንጎው ፊት ቀርቤ በነበረበት ጊዜ ያገኙብኝ ወንጀል ካለ ይናገሩ፤
21 በመካከላቸው በቆምሁበት ጊዜ ስለ ሙታን ትንሣኤ ከተናገርሁት አንድ ነገር በስተቀር ዛሬ ተከስሼ የቀረብሁበት ሌላ ነገር የለም።”
22 ፊልክስ ግን የጌታን መንገድ በሚገባ ዐውቆ ስለ ነበር፣ “የጦር አዛዡ ሉስዮስ ሲመጣ ለጒዳያችሁ ውሳኔ እሰጣለሁ” ብሎ ነገሩን በቀጠሮ አሳደረው።
23 ከዚያም ለጳውሎስ መጠነኛ ነጻነት እየሰጠ እንዲጠብቀውና ወዳጆቹም ገብተው እንዲጠይቁት ፈቃድ እንዲሰጣቸው የመቶ አለቃውን አዘዘው።
24 ከጥቂት ቀን በኋላ፣ ፊልክስ ከአይሁ ዳዊት ሚስቱ ከድሩሲላ ጋር መጣ፤ ጳውሎስንም አስጠርቶ በክርስቶስ ኢየሱስ ስለ ማመን ሲናገር አዳመጠው።
25 ጳውሎስ ስለ ጽድቅና ራስን ስለ መግዛት ስለሚመጣውም ፍርድ በሚናገርበት ጊዜ ግን ፊልክስ ፈርቶ፣ “ለጊዜው ይህ ይበቃል፤ ወደ ፊት ሲመቸኝ አስጠራሃለሁ፤ አሁን ልትሄድ ትችላለህ” አለው።
26 ደግሞም ከጳውሎስ ጉቦ ለመቀበል ተስፋ ያደርግ ስለ ነበር፣ በየጊዜው እያስጠራ ያነጋግረው ነበር።
27 ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላም፣ ፊልክስ በጶርቅዮስ ፊስጦስ ተተካ፤ ፊልክስም አይሁድን ለማስደሰት ሲል፣ ጳውሎስን እንደ ታሰረ ተወው።