ሐዋርያት ሥራ 10 NASV

ቆርኔሌዎስ ጴጥሮስን አስጠራ

1 በቂሳርያ፣ ‘የኢጣሊያ ክፍለ ጦር’ በሚባለው ሰራዊት ውስጥ የመቶ አለቃ የሆነ ቆርኔሌዎስ የተባለ አንድ ሰው ነበረ።

2 እርሱም ከመላው ቤተ ሰቡ ጋር በመንፈሳዊ ነገር የተጋና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ለሰዎች እጅግ ምጽዋት የሚሰጥ፣ አዘውትሮ ወደ እግዚአብሔር የሚጸልይ ነበር።

3 አንድ ቀን፣ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ የእግዚአብሔር መልአክ በራእይ ወደ እርሱ መጥቶ፣ “ቆርኔሌዎስ ሆይ!” ሲለው በግልጽ አየ።

4 ቆርኔሌዎስም በድንጋጤ ትኵር ብሎ እያየው፣ “ጌታ ሆይ፤ ምንድን ነው?” አለው።መልአኩም እንዲህ አለው፤ “ጸሎትህና ምጽዋትህ ለመታሰቢያነት ወደ እግዚአብሔር ፊት አርጎልሃል።

5 አሁንም ሰዎች ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣው፤

6 እርሱም በባሕሩ አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ዐርፎአል።”

7 ቆርኔሌዎስም፣ ያነጋገረው መልአክ ተለይቶት ከሄደ በኋላ፣ ከአገልጋዮቹ ሁለቱን፣ እንዲሁም በመንፈሳዊ ነገር የተጋና ለእርሱ ታማኝ የሆነውን አንዱን ወታደር አስጠራ፤

8 የሆነውንም ነገር ሁሉ ከነገራቸው በኋላ ወደ ኢዮጴ ላካቸው።

ጴጥሮስ ያየው ራእይ

9 የተላኩትም ሰዎች በማግስቱ ወደ ከተማዪቱ እንደ ተቃረቡ፣ ጴጥሮስ እኩለ ቀን ገደማ ሲሆን፣ ለመጸለይ ወደ ሰገነት ወጣ።

10 በዚያን ጊዜም ስለ ተራበ የሚበላ ነገር ፈለገ፤ ምግብ እየተዘጋጀ ሳለም አሸለበውና በተመስጦ ውስጥ ሆነ፤

11 ሰማይም ተከፍቶ አንድ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራቱ ማእዘን ተይዞ ወደ ምድር ሲወርድ አየ።

12 በጨርቁም ላይ አራት እግር ያላቸው የተለያዩ እንስሳት፣ በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና በአየር የሚበሩ አዕዋፍ ነበሩበት።

13 በዚህ ጊዜ፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ ተነሣ፤ እነዚህን ዐርደህ ብላ” የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ።

14 ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ፤ ይህማ አይሆንም፤ እኔ ያልተቀደሰ ወይም ርኵስ ነገር ፈጽሞ በልቼ አላውቅምና” አለ።

15 ያም ድምፅ እንደ ገና ለሁለተኛ ጊዜ ወደ እርሱ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ እንደ ርኵስ አትቍጠረው” አለው።

16 ይህም ሦስት ጊዜ ተደጋገመ፤ ጨር ቁም ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ተወሰደ።

17 ጴጥሮስም ስላየው ራእይ ትርጒም እጅግ ተጨንቆ በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች የስምዖንን ቤት ፈልገው ካገኙ በኋላ መጥተው በሩ ላይ ቆሙ፤

18 ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው ጴጥሮስ የተባለው ስምዖን እዚያ ይኖር እንደሆነ ጠየቁ።

19 ጴጥሮስ የራእዩን ነገር በማሰላሰል ላይ ሳለ፣ መንፈስ እንዲህ አለው፤ “እነሆ፤ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል፤

20 ስለዚህ ተነሥተህ ውረድ፤ የላክኋቸውም እኔ ስለ ሆንሁ ሳትጠራጠር ከእነርሱ ጋር ሂድ።”

21 ጴጥሮስም ወርዶ፣ “እነሆ፤ የምትፈልጉት ሰው እኔ ነኝ፤ የመጣችሁበት ጒዳይ ምንድን ነው?” አላቸው።

22 ሰዎቹ፣ “የመጣነው ቆርኔሌዎስ ከተባለው መቶ አለቃ ዘንድ ነው፤ እርሱም ጻድቅና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ በአይሁድም ሕዝብ ሁሉ ዘንድ የተከበረ ሰው ነው። አንተን ወደ ቤቱ እንዲያስመጣህና የምትለውን እንዲሰማ ቅዱስ መልአክ ነግሮታል” አሉት።

23 ጴጥሮስም ሰዎቹን ሊያስተናግዳቸው ወደ ቤት አስገባቸው።ጴጥሮስም በማግስቱ ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ ከኢዮጴ የመጡ አንዳንድ ወንድሞችም አብረውት ሄዱ፤

ጴጥሮስ በቆርኔሌዎስ ቤት

24 በሚቀጥለው ቀን ቂሳርያ ገባ። ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ሰብስቦ ይጠብቃቸው ነበር።

25 ጴጥሮስም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለው፤ እግሩም ላይ ወድቆ ሰገደለት።

26 ጴጥሮስ ግን፣ “እኔም እንዳንተው ሰው ነኝና ተነሥ!” ብሎ አስነሣው።

27 ጴጥሮስም እያነጋገረው አብሮት ሲገባ ብዙ ሰው ተሰብስቦ አገኘ፤

28 እንዲህም አላቸው፤ “አንድ አይሁዳዊ ከሌላ ወገን ጋር እንዲተባበር ወይም እንዲቀራረብ ሕጋችን እንደማይፈቅድ ራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እኔ ማንንም ርኵስ ወይም ያልተቀደሰ ነው እንዳልል እግዚአብሔር አሳይቶኛል፤

29 ስለዚህም በተጠራሁ ጊዜ፣ እነሆ ሳላመነታ መጣሁ፤ እንግዲህ፣ ለምን እንደጠራችሁኝ ማወቅ እፈልጋለሁ።”

30 ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፤ “ከአራት ቀን በፊት በዚህ ጊዜ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በቤቴ ሆኜ እጸልይ ነበር፤ ድንገትም ብሩህ ልብስ የለበሰ ሰው መጥቶ በፊቴ ቆመና

31 እንዲህ አለኝ፤ ‘ቆርኔሌዎስ ሆይ፤ ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ምጽዋትህም ለመታሰቢያነት በእግዚአብሔር ፊት ደርሶአል።

32 ሰዎችን ወደ ኢዮጴ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣ፤ እርሱም በባሕር አጠገብ ባለው በቍርበት ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት ዐርፎአል።’

33 እኔም ወዲያው ላኩብህ፤ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። እንግዲህ እኛ ሁላችን ጌታ ያዘዘህን ስትነግረን ለመስማት በእግዚአብሔር ፊት አለን።

34 ጴጥሮስም እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፤ “እግዚአብሔር ለማንም እንደማያዳላ በርግጥ ተረድቻለሁ፤

35 ነገር ግን እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ከየትኛውም ወገን ቢሆኑ ይቀበላቸዋል።

36 እግዚአብሔር፣ የሁሉ ጌታ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የላከውም የሰላም የምሥራች መልእክት ይኸው ነው።

37 ዮሐንስ ከሰበከው ጥምቀት በኋላ ከገሊላ ጀምሮ በመላው ይሁዳ የሆነውን ታውቃላችሁ፤

38 እግዚአብሔር የናዝሬቱን ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስና በኀይል ቀባው፤ እርሱም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ በደረሰበት ሁሉ መልካም እያደረገ በዲያብሎስ ሥልጣን ሥር የነበሩትን ሁሉ ፈወሰ።

39 “እርሱ በአይሁድ አገርና በኢየሩሳሌም ላደረገው ሁሉ እኛ ምስክሮች ነን፤ ደግሞም ሰዎች እርሱን በዕንጨት ላይ ሰቅለው ገደሉት።

40 እግዚአብሔር ግን በሦስተኛው ቀን ከሙታን አስነሣው፤ እንዲታይም አደረገው፤

41 የታየውም ለሁሉ ሰው ሳይሆን፣ ከሙታን ከተነሣ በኋላ አብረነው ለበላንና ለጠጣን፣ እግዚአብሔርም አስቀድሞ ለመረጠን ለእኛ ለምስክሮቹ ነው።

42 ለሕዝቡ እንድንሰብክና በሕያዋንና በሙታንም ላይ እንዲፈርድ እግዚአብሔር የሾመው እርሱ መሆኑን እንድንመሰክር እርሱ ራሱ አዘዘን፤

43 በእርሱም የሚያምን ሁሉ በስሙ የኀጢአትን ስርየት እንደሚቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል።”

44 ጴጥሮስ ይህን እየተናገረ ሳለ፣ ቃሉን በሰሙት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደባቸው።

45 ከጴጥሮስ ጋር የመጡት፣ ከተገረዙት ወገን የሆኑት አማኞች፣ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በአሕዛብም ላይ ደግሞ መፍሰሱን ሲያዩ ተገረሙ፤

46 ይኸውም በልሳን ሲናገሩና እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ስለ ሰሟቸው ነው።በዚያ ጊዜ ጴጥሮስ እንዲህ አለ፤

47 “እነዚህ ሰዎች እንደ እኛ መንፈስ ቅዱስን ስለ ተቀበሉ፣ እንግዲህ በውሃ እንዳይጠመቁ የሚከለክላቸው ማን ነው?”

48 ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲጠመቁ አዘዛቸው። ከዚህ በኋላ፣ ጴጥሮስ ጥቂት ቀን ከእነርሱ ጋር እንዲቀመጥ ለመኑት።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28