18 ይህንም ብዙ ቀን ደጋገመችው፤ ጳውሎስ ግን በዚህ እጅግ በመታወኩ ዘወር ብሎ ያን መንፈስ፣ “ከእርሷ እንድትወጣ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ” አለው፤ መንፈሱም በዚያው ቅጽበት ወጣላት።
19 አሳዳሪዎቿም የገንዘብ ማግኛ ተስፋቸው ወጥቶ መሄዱን በተረዱ ጊዜ፣ ጳውሎስንና ሲላስን ይዘው እየጐተቱ ባለ ሥልጣኖች ወዳሉበት ወደ ገበያ ቦታ አመጧቸው።
20 ገዦቹም ፊት አቅርበዋቸው እንዲህ አሉ፤ “እነዚህ ሰዎች አይሁድ ሆነው ሳሉ፣ ከተማችንን አውከዋል፤
21 ደግሞም እኛ ሮማውያን መቀበል ወይም መፈጸም የማይገባንን ልማድ በሕዝቡ መካከል ይነዛሉ።”
22 ሕዝቡም ተባብረው በጳውሎስና በሲላስ ላይ ተነሡባቸው፤ ገዦቹም ልብሳቸው ተገፎ በበትር እንዲደበደቡ አዘዙ።
23 ክፉኛ ከተደበደቡ በኋላም ወደ ወህኒ ቤት አስገቧቸው፤ የወህኒ ቤት ጠባቂውም ተጠንቅቆ እንዲጠብቃቸው አዘዙት።
24 እርሱም ይህን የመሰለ ትእዛዝ ከተቀበለ በኋላ፣ ወደ ወህኒ ቤቱ ውስጠኛ ክፍል አስገብቶ እግራቸውን ከግንድ ጋር አጣብቆ አሰራቸው።