34 ሕዝቡም ከፊሉ አንድ ነገር ሲናገር፣ ከፊሉ ደግሞ ሌላ ይናገር ነበር፤ ከጫጫታው የተነሣም አዛዡ ምንም ነገር ሊሰማ አልቻለም፤ ስለዚህ ጳውሎስ ወደ ጦር ሰፈር እንዲወሰድ አዘዘ።
35 ከሕዝቡ ሁካታ የተነሣ፣ ጳውሎስ ወደ መውጫው ደረጃ ሲደርስ ወታደሮቹ ይሸከሙት ዘንድ ግድ ሆነባቸው።
36 ከኋላ የተከተለውም ሕዝብ፣ “አስወግደው!” እያለ ይጮኽ ነበር።
37 ወታደሮቹ ወደ ጦር ሰፈር ይዘውት ሊሄዱ ሲሉ፣ ጳውሎስ ጦር አዛዡን፣ “አንድ ነገር እንድነግርህ ፍቀድልኝ?” አለው።አዛዡም እንዲህ አለው፤ “የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህ?
38 አንተ ከዚህ ቀደም ዐመፅ አስነሥተህ፣ አራት ሺህ ነፍሰ ገዳዮችን ወደ በረሓ ያሸፈትኸው ግብፃዊ አይደለህምን?”
39 ጳውሎስም፣ “እኔስ በኪልቅያ ያለችው የታዋቂዋ የጠርሴስ ከተማ ነዋሪ የሆንሁ አይሁዳዊ ነኝ፤ ለሕዝቡ ንግግር እንዳደርግ ፍቀድልኝ” አለው።
40 ጳውሎስም የጦር አዛዡን ካስፈቀደ በኋላ፣ በደረጃው ላይ ቆሞ ሕዝቡን በእጁ ጠቀሰ፤ ሁሉም ጸጥ ባሉ ጊዜ፣ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ አለ፤