12 ፊስጦስ ከመማክርቱ ጋር ከተመካከረ በኋላ፣ “ወደ ቄሳር ይግባኝ ስላልህ፣ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ” አለው።
13 ከጥቂት ቀንም በኋላ፣ ንጉሥ አግሪጳና በርኒቄ ፊስጦስን እጅ ሊነሡ ወደ ቂሳርያ ወረዱ፤
14 በዚያም ብዙ ቀን ተቀመጡ፤ ፊስጦስም የጳውሎስን ጒዳይ አንሥቶ ለንጉሡ እንዲህ አለው፤ “ፊልክስ በእስር ቤት የተወው አንድ ሰው እዚህ አለ፤
15 ወደ ኢየሩሳሌም በሄድሁ ጊዜ፣ የካህናት አለቆችና የአይሁድ ሽማግሌዎች እንድፈርድበት ከሰውት ነበር።
16 “እኔም፣ ተከሳሽ በከሳሾቹ ፊት ቆሞ ለተከሰሰበት ነገር መልስ ለመስጠት ዕድል ሳያገኝ፣ አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ልማድ እንዳልሆነ ነገርኋቸው።
17 ስለዚህ ከሳሾቹ ከእኔ ጋር ወደዚህ በመጡ ጊዜ፣ ጒዳዩን ሳላጓትት በማግስቱ ችሎት ተቀምጬ ያን ሰው እንዲያቀርቡት አዘዝሁ።
18 ከሳሾቹም ተነሥተው በመቆም ሲናገሩ፣ እኔ ያሰብሁትን ያህል ከባድ ክስ አላቀረ ቡበትም፤