38 የቤተ መቅደሱም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ።
39 በኢየሱስ ትይዩ ቆሞ የነበረውም የመቶ አለቃ እንደዚህ ጮኾ ነፍሱን ሲሰጥ ባየ ጊዜ፣ “ይህ ሰው በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ነበር” አለ።
40 በዚህ ጊዜ ሴቶች ከሩቅ ሆነው ይመለከቱ ነበር፤ ከእነርሱም መካከል መግደላዊት ማርያም፣ የታናሹ ያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም፣ እንዲሁም ሰሎሜ ነበሩ፤
41 እነዚህ ሴቶች በገሊላ ሲከተሉትና ሲያገለግሉት የነበሩ ናቸው፤ ደግሞም አብረውት ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሌሎች ብዙ ሴቶች ነበሩ።
42 ጊዜው እየመሸ መጥቶ የሰንበት ዋዜማ ይኸውም የመዘጋጀት ቀን ሆነ፤
43 የተከበረ የሸንጎ አባልና የእግዚአብሔርን መንግሥት ይጠባበቅ የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ በድፍረት ወደ ጲላጦስ ሄዶ የኢየሱስን ሥጋ ለመነው።
44 ጲላጦስም እንዲህ በቶሎ መሞቱን ሲሰማ ተደነቀ፤ የመቶ አለቃውንም ጠርቶ ከሞተ ምን ያህል ጊዜ እንደሆነ ጠየቀው፤