1 ከቤተ መቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፣ “መምህር ሆይ፤ ድንጋዮቹ እንዴት እንደሆኑ፣ ሕንጻውም እንዴት ውብ እንደሆነ እይ” አለው።
2 ኢየሱስም መልሶ፣ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? አንዱ ድንጋይ በሌላው ላይ እንደሆነ አይቀርም፤ ሁሉም ፈራሽ ነው” አለው።
3 ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ትይዩ፣ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤
4 “ይህ መቼ እንደሚሆን ንገረን፤ የዚህስ ሁሉ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድን ነው?”
5 ኢየሱስም እንዲህ ይላቸው ጀመር፤ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤
6 ብዙዎች፣ ‘እኔ እርሱ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ።
7 ስለ ጦርነትና ስለ ጦርነት ወሬ በምትሰሙበት ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህማ መሆን አለበት፤ ፍጻሜው ግን ገና ነው።
8 ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥት በመንግሥት ላይ ይነሣል፤ በብዙ ቦታም የመሬት መንቀጥቀጥና ራብ ይሆናል፤ እነዚህ ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።
9 “ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ለአካባቢ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጧችኋል፤ በምኵራብ ይገርፏችኋል፤ ምስክር ትሆኑም ዘንድ በእኔ ምክንያት በገዦችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ።
10 አስቀድሞ ግን ወንጌል ለሕዝብ ሁሉ መሰበክ አለበት።
11 ተይዛችሁ ለፍርድ በምትቀርቡበት ጊዜ፣ በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ እንጂ ምን እንናገራለን በማለት አስቀድማችሁ አትጨነቁ፤ የሚናገረው መንፈስ ቅዱስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።
12 “ወንድም ወንድሙን፣ አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያምፃሉ፤ ይገድሏቸዋልም።
13 በእኔ ምክንያት በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻው የሚጸና ግን ይድናል።
14 “ ‘የጥፋት ርኵሰት’ ስፍራው ባልሆነ ቦታ ቆሞ በምታዩት ጊዜ አንባቢው ያስተውል፤ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፤
15 በቤቱ ጣራ ላይ ያለ አይውረድ፤ ንብረቱንም ለማውጣት ወደ ቤቱ አይግባ፤
16 በእርሻ ቦታ ያለ ልብሱን ለመውሰድ አይመለስ።
17 በእነዚያ ቀናት ለነፍሰ ጡሮችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው!
18 ይህም በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤
19 በመጀመሪያ እግዚአብሔር ፍጥረትን ከፈጠረበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ፣ እንዲሁ ደግሞም ወደ ፊት አቻ የሌለው ታላቅ መከራ ይሆናልና።
20 ጌታ ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ ማንም ባልዳነ ነበር፤ ስለ መረጣቸው ስለ ምርጦቹ ሲል ግን ቀኖቹን አሳጥሮአል።
21 በዚያን ጊዜ ማንም፣ ‘እነሆ፤ ክርስቶስ እዚህ ነው?’ ቢላችሁ ወይም፣ ‘እነሆ፤ እዚያ ነው’ ቢላችሁ አትመኑ።
22 ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት ተነሥተው፣ ምልክቶችንና ድንቆችን በማድረግ፣ ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ ያስታሉ።
23 ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ጊዜው ሳይደርስ ሁሉን ነግሬአችኋለሁ።
24 “በዚያን ጊዜ፣ ከመከራው በኋላ ‘ፀሓይ ትጨልማለች፣ “ ‘ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤
25 ከዋክብት ከሰማይ ይረግፋሉ፤ የሰማይ ኀይላትም ይናወጣሉ።’
26 “በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በታላቅ ኀይልና ግርማ በደመና ሲመጣ ያዩታል።
27 እርሱም መላእክቱን ልኮ ከአራቱ ነፋሳት፣ ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማያት ዳርቻ ምርጦቹን ይሰበስባል።
28 “ምሳሌውን ከበለስ ተማሩ፤ ቅርንጫፏ ሲለመልም፣ ቅጠሏ ሲያቈጠቍጥ በጋ እንደ ተቃረበ ታውቃላችሁ፤
29 እንዲሁ ደግሞ እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸውን ስታዩ እንደ ቀረበ፣ በደጅም እንደሆነ ዕወቁ።
30 እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች እስከሚፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም፤
31 ሰማይና ምድር ያልፋሉ፣ ቃሌ ግን አያልፍም።
32 “ነገር ግን ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያችም ሰዓት ከአብ በቀር፣ የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ወልድም ቢሆን፣ ማንም አያውቅም።
33 ስለዚህ ጊዜው መቼ እንደሚሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፣ ጸልዩም።
34 ይህም ቤቱን ለአገልጋዮቹ ትቶ፣ እያንዳንዱን አገልጋይ በየሥራ ድርሻው ላይ አሰማርቶ፣ በረኛው ነቅቶ እንዲጠብቅ አዝዞ የሄደውን ሰው ይመስላል።
35 እንግዲህ የቤቱ ባለቤት በምሽት ወይም በውድቅት፣ በዶሮ ጩኸት ወይም ጎሕ ሲቀድ እንደሚመጣ አታውቁምና ተግታችሁ ጠብቁ፤
36 ድንገት ሲመጣ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ፤
37 ለእናንተ የምነግራችሁን ለሰው ሁሉ እናገራለሁ፤ ተግታችሁ ጠብቁ!”