1 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ወደ ገዛ አገሩ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።
2 ሰንበትም በደረሰ ጊዜ፣ በምኵራብ ያስተምር ጀመር፤ የሰሙትም ብዙ ሰዎች፣ ተደነቁ።እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “ይህ ሰው እነዚህን ነገሮች ከየት አገኛቸው? ይህ የተሰጠው ጥበብ ምንድን ነው? ደግሞም እነዚህ ታምራት እንዴት በእጁ ይደረጋሉ!
3 ይህ ዐናጢው አይደለምን? የማርያም ልጅ፣ የያዕቆብና የዮሴፍ፣ የይሁዳና የስምዖን ወንድም አይደለምን? እኅቶቹስ እዚሁ እኛው ዘንድ አይደሉምን?” ከዚህም የተነሣ ተሰናከሉበት።
4 ኢየሱስም፣ “ነቢይ የማይከበረው በገዛ አገሩ፣ በዘመዶቹ መካከልና በቤተ ሰቡ ዘንድ ብቻ ነው” አላቸው።
5 እዚያም በጥቂት ሕመምተኞች ላይ እጁን ጭኖ ከመፈወሱ በስተቀር ምንም ታምራት ሊሠራ አልቻለም፤
6 ባለማመናቸውም ተደነቀ።ከዚያም ኢየሱስ በየመንደሩ እየተዘዋወረ ያስተምር ነበር።
7 ዐሥራ ሁለቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፣ ሁለት ሁለቱን ላካቸው፤ በርኵሳን መናፍስትም ላይ ሥልጣን ሰጣቸው።
8 ይህንንም ትእዛዝ ሰጣቸው፤ “ለመንገዳችሁ ከበትር በስተቀር፣ እንጀራ ወይም ከረጢት ወይም ደግሞ ገንዘብ በመቀነታችሁ አትያዙ፤
9 ጫማ አድርጉ፤ ነገር ግን ሁለት እጀ ጠባብ አትልበሱ፤
10 ወደ አንድ ቤት በምትገቡበት ጊዜ ከዚያች ከተማ እስክትወጡ ድረስ እዚያው ቈዩ፤
11 የትኛውም ቦታ የማይቀበላችሁ ወይም የማይሰማችሁ ከሆነ፣ ከዚያ ስፍራ ስትወጡ ምስክር እንዲሆንባቸው ከእግራችሁ ሥር ያለውን ትቢያ በዚያ አራግፉ።”
12 እነርሱም ከዚያ ወጥተው፤ ሰዎች ንስሓ እንዲገቡ ሰበኩ፤
13 ብዙ አጋንንት አስወጡ፤ ብዙ ሕመምተኞችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱ።
14 የኢየሱስ ስም እየታወቀ በመምጣቱ፣ ንጉሥ ሄሮድስ ይህንኑ ሰማ። አንዳንዶችም፣ “የዚህ ዐይነት ታምር በእርሱ የሚሠራው መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ቢነሣ ነው” ይሉ ነበር።
15 ሌሎቹም፣ “ኤልያስ ነው” አሉ።አንዳንዶች ደግሞ፣ “ከቀደምት ነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው” ይሉ ነበር።
16 ሄሮድስ ነገሩን ሲሰማ ግን፣ “እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል!” አለ።
17 ሄሮድስ ራሱ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን በማግባቱ ምክንያት፣ ተይዞ እንዲታሰር ትእዛዝ በመስጠት ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገብቶት ነበር
18 ዮሐንስ ሄሮድስን፣ “የወንድምህን ሚስት ታገባት ዘንድ ሕግ ይከለክልሃል” ይለው ነበርና።
19 ሄሮድያዳም በዚህ ቂም ይዛበት ልታስገድለው ፈለገች፤ ነገር ግን አልሆነላትም።
20 ምክንያቱም ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው መሆኑን ሄሮድስ በማወቁ ይፈራውና ይጠብቀው ነበር። ዮሐንስ የሚናገረውን ሲሰማ ሄሮድስ ቢታወክም በደስታ ያደምጠው ነበር።
21 በመጨረሻም አመቺ ቀን መጣ። ሄሮድስ በተወለደበት ዕለት ለከፍተኛ ሹማምቱ፣ ለጦር አዛዦቹና በገሊላ ለታወቁ ታላላቅ ሰዎች ግብዣ አደረገ።
22 የሄሮድያዳም ልጅ ገብታ በዘፈነች ጊዜ ሄሮድስንና ተጋባዦቹን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናዪቱን፣ “የምትፈልጊውን ሁሉ ጠይቂኝ እሰጥሻለሁ” አላት።
23 ደግሞም “እስከ መንግሥቴ እኩሌታ ድረስ እንኳ ቢሆን፣ የምትጠይቂኝን ሁሉ እሰጥሻለሁ” ሲል በመሓላ ቃል ገባላት።
24 እርሷም ወጥታ እናቷን፣ “ምን ልለምነው?” አለቻት።እናቷም፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ” አለቻት።
25 ብላቴናዪቱም ወዲያው ፈጥና ወደ ንጉሡ በመመለስ፣ “የመጥምቁ ዮሐንስን ራስ አሁን በሳሕን እንድትሰጠኝ እፈልጋለሁ” አለችው።
26 ንጉሡ በነገሩ እጅግ አዘነ፤ በተጋበዙት እንግዶች ፊት የመሐላ ቃሉን ለማጠፍ አልፈለገም።
27 ስለዚህ አንዱን ወታደር በፍጥነት ልኮ፣ የዮሐንስን ራስ ቈርጦ እንዲያመጣ አዘዘው፤ እርሱም ሄዶ በወህኒ ቤቱ ውስጥ ራሱን ቈረጠ፤
28 በሳሕን አምጥቶ ለብላቴናዪቱ ሰጣት፤ ብላቴናዪቱም ለእናትዋ ሰጠች።
29 የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትም ይህን እንደ ሰሙ መጡ፤ ሬሳውንም ወስደው ቀበሩት።
30 ሐዋርያትም በኢየሱስ ዙሪያ ተሰብስበው የሠሩትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት።
31 ብዙ ሰዎች ይመጡና ይሄዱ ስለ ነበር ምግብ እንኳ ለመብላት ጊዜ ስላልነበራቸው፣ “እስቲ ብቻችሁን ከእኔ ጋር ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ እንሂድና ጥቂት ዕረፉ” አላቸው።
32 ስለዚህ ብቻቸውን ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ በጀልባ ሄዱ።
33 እነርሱም ሲሄዱ ብዙ ሰዎች አይተው ዐወቋቸው፤ ከከተሞችም ሁሉ በእግር እየሮጡ ቀድመዋቸው ደረሱ።
34 ኢየሱስ ከጀልባዋ በሚወርድበት ጊዜ ብዙ ሕዝብ ተሰብስቦ አየ፤ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩም አዘነላቸው፤ ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር።
35 በዚህ ጊዜ ቀኑ እየመሸ በመሄዱ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው እንዲህ አሉት፤ “ይህ ቦታ ምድረ በዳ ነው፤ ቀኑም መሽቶአል፤
36 በአካባቢው ሰው ወዳለበት መንደር ሄደው የሚበላ ነገር ገዝተው እንዲመገቡ ሕዝቡን አሰናብታቸው።”
37 እርሱ ግን መልሶ፣ “የሚበሉትን እናንተው ስጧቸው” አላቸው።እነርሱም፣ “ሄደን በሁለት መቶ ዲናር እንጀራ ገዝተን የሚበሉትን እንስጣቸውን?” አሉት።
38 እርሱም፣ “ስንት እንጀራ አላችሁ? እስቲ ሄዳችሁ እዩ” አላቸው።አይተውም፣ “አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ” አሉት።
39 ከዚያም፣ ሕዝቡን በለመለመ ሣር ላይ በቡድን በቡድን እንዲያስቀምጡ አዘዛቸው።
40 ሕዝቡም መቶ መቶና አምሳ አምሳ ሆነው በቡድን በቡድን ተቀመጡ።
41 እርሱም አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ በማየት ባረከ፤ እንጀራውንም ቈርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፤ ሁለቱንም ዓሣ ለሁሉም አካፈለ።
42 ሁሉም በልተው ጠገቡ፤
43 ደቀ መዛሙርቱም ከተበላው እንጀራና ዓሣ፣ ዐሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ ፍርፋሪ አነሡ።
44 እንጀራውንም የበሉት አምስት ሺህ ወንዶች ነበሩ።
45 ወዲያውም እርሱ ሕዝቡን እያሰናበተ ሳለ፣ ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ወደ ቤተ ሳይዳ ቀድመውት እንዲሻገሩ አዘዛቸው፤
46 ከዚያም ትቶአቸው ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ።
47 በመሸም ጊዜ ጀልባዋ ባሕሩ መካከል ነበረች፤ እርሱም ብቻውን በምድር ላይ ነበር።
48 ነፋስ በርትቶባቸው ስለ ነበር፣ ደቀ መዛሙርቱ ከመቅዘፊያው ጋር ሲታገሉ አያቸው፤ በአራተኛውም ክፍለ ሌሊት ገደማ፣ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ በአጠገባቸውም ዐልፎ ሊሄድ ነበር።
49 ነገር ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሐት መስሎአቸው ጮኹ፤
50 ሁሉም እርሱን ባዩት ጊዜ ደንግጠው ነበርና። እርሱም ወዲያውኑ አነጋገራቸውና፣ “አይዞአችሁ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ!” አላቸው።
51 እርሱም በጀልባዋ ላይ ወጥቶ አብሮአቸው ሆነ፤ ነፋሱም ተወ፤ እነርሱም እጅግ ተደነቁ፤
52 የእንጀራውን ታምር አላስተዋሉም ነበርና፤ ልባቸውም ደንድኖ ነበር።
53 በተሻገሩም ጊዜ፣ ጌንሴሬጥ ደርሰው ወረዱ፤ ጀልባዋንም እዚያው አቆሙ።
54 ወዲያው እንደ ወረዱም፣ ሕዝቡ ኢየሱስን ዐወቁት፤
55 ወደ አካባቢውም ሁሉ በመሮጥ ሕመምተኞችን በዐልጋ ላይ እየተሸከሙ እርሱ ወደሚገኝበት ስፍራ ሁሉ ያመጡ ነበር።
56 በየደረሰበት መንደር ወይም ከተማ ወይም ገጠር ሁሉ ሕመምተኞችን በየአደባባዩ እያስቀመጡ የልብሱን ጫፍ እንኳ ለመንካት ይለምኑት ነበር፤ የነኩትም ሁሉ ይድኑ ነበር።