27 የሚቀረው ግን የሚያስፈራ ፍርድና የእግዚአብሔርን ጠላቶች የሚበላ ብርቱ እሳት መጠበቅ ብቻ ነው።
28 የሙሴን ሕግ የናቀ ማንኛውም ሰው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች ከመሰከሩበት ያለ ምሕረት ይገደል ነበር።
29 ታዲያ የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ፣ የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ተራ ነገር የቈጠረ፣ የጸጋንም መንፈስ ያክፋፋ እንደ ምን ያለ የባሰ ቅጣት ይገባው ይመስላችኋል?
30 “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ያለውን እናውቀዋለንና፤ ደግሞም፣ “ጌታ በሕዝቡ ላይ ይፈርዳል” ይላል።
31 በሕያው እግዚአብሔር እጅ መውደቅ እጅግ የሚያስፈራ ነው።
32 ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ፣ በመከራ ውስጥ በብርቱ ተጋድሎ ጸንታችሁ የቆማችሁበትን የቀድሞውን ዘመን ዐስቡ።
33 አንዳንድ ጊዜ በአደባባይ ለስድብና ለስደት ተጋልጣችሁ ነበር፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ እንደዚህ ያለ መከራ ከደረሰባቸው ሰዎች ጋር አብራችሁ መከራን ተቀብላችኋል።