ዮሐንስ 2 NASV

ኢየሱስ ውሃን የወይን ጠጅ አደረገ

1 በሦስተኛው ቀን፣ በገሊላ አውራጃ፣ በቃና ከተማ ሰርግ ነበር፤ የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤

2 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱም ወደ ሰርጉ ተጠርተው ነበር።

3 የወይን ጠጅ ባለቀ ጊዜም የኢየሱስ እናት፣ “የወይን ጠጅ እኮ አለቀባቸው” አለችው።

4 ኢየሱስም፣ “አንቺ ሴት ሆይ፤ ምን አድርግ ትይኛለሽ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት።

5 እናቱም በዚያ የነበሩትን አገልጋዮች፣ “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” አለቻቸው።

6 በአይሁድ የመንጻት ሥርዐት መሠረት፣ ከሰባ አምስት እስከ አንድ መቶ ዐሥራ አምስት ሊትር የሚይዙ ከድንጋይ የተሠሩ ስድስት ጋኖች በዚያ ነበሩ።

7 ኢየሱስ አገልጋዮቹን፣ “ጋኖቹን ውሃ ሙሏቸው” አላቸው፤ እነርሱም፣ ጋኖቹን እስከ አፋቸው ሞሏቸው።

8 እርሱም፣ “ከላዩ ቀድታችሁ ለድግሱ ኀላፊ ስጡት” አላቸው።እነርሱም እንዳዘዛቸው አደረጉ።

9 የድግሱ ኀላፊም ወደ ወይን ጠጅ የተለወጠውን ውሃ ቀመሰ፤ ሆኖም ከየት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውሃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር። እርሱም ሙሽራውን ለብቻው ጠርቶ፣

10 “ሰው ሁሉ በመጀመሪያ የሚያቀርበው ጥሩውን የወይን ጠጅ ነው፤ እንግዶቹም ብዙ ከጠጡ በኋላ መናኛውን የወይን ጠጅ ያቀርባል፤ አንተ ግን ጥሩውን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቈይተሃል” አለው።

11 ኢየሱስም ይህን የታምራዊ ምልክቶቹ መጀመሪያ በገሊላ አውራጃ በቃና ከተማ አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።

ኢየሱስ ቤተ መቅደስን አጠራ

12 ከዚህ በኋላ ከእናቱ፣ ከወንድሞቹና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፤ በዚያም ጥቂት ቀን ተቀመጡ።

13 የአይሁድ ፋሲካም እንደ ተቃረበ፣ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።

14 በቤተ መቅደሱ አደባባይ ከብቶችን፣ በጎችንና ርግቦችን የሚሸጡ እንዲሁም ተቀምጠው የገንዘብ ምን ዛሪ የሚያከናውኑ ሰዎች አገኘ።

15 የገመድ ጅራፍ አበጅቶ በጎችንና ከብቶችን ሁሉ ከቤተ መቅደሱ ግቢ አባረረ፤ የመንዛሪዎችን ገንዘብ በተነ፤ ጠረጴዞቻቸውንም ገለበጠ።

16 ርግብ ሻጮችንም፣ “እነዚህን ከዚህ አስወጧቸው፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት!” አላቸው።

17 ደቀ መዛሙርቱም፣ “ለቤትህ ያለኝ ቅናት ያቃጥለኛል” ተብሎ የተጻፈው ትዝ አላቸው።

18 አይሁድም፣ “ይህን ሁሉ ለማድረግ ሥልጣን እንዳለህ የሚያረጋግጥ ምን ታምራዊ ምልክት ታሳየናለህ?” አሉት።

19 ኢየሱስም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፤ እኔም በሦስት ቀን መልሼ አነሣዋለሁ” ብሎ መለሰላቸው።

20 አይሁድም፣ “ይህን ቤተ መቅደስ ለመሥራት አርባ ስድስት ዓመት ፈጅቶአል፤ ታዲያ አንተ እንዴት በሦስት ቀን መልሰህ ታነሣዋለህ?” አሉት።

21 ቤተ መቅደስ ሲል ግን፣ ስለ ገዛ ሰውነቱ መናገሩ ነበር።

22 ከሙታንም ከተነሣ በኋላ፣ ደቀ መዛሙርቱ ምን እንደ ተናገረ አስታወሱ፤ መጻሕፍትንና ኢየሱስ ያለውንም ቃል አመኑ።

23 በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ፣ ብዙ ሰዎች ያደረገውን ታምራት አይተው በስሙ አመኑ፤

24 ኢየሱስ ግን ሰውን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ አይታመንባቸውም ነበር፤

25 በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ ስለ ነበር፣ ማንም ስለ ሰው እንዲመሰክርለት አላስፈለገውም።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21