1 ከዚህ በተረፈ ወንድሞቼ ሆይ፤ በጌታ ደስ ይበላችሁ። ያንኑ ደግሜ ብጽፍላችሁ እኔ አይሰለቸኝም፤ ለእናንተም ይጠቅማችኋል።
2 ከእነዚያ ውሾች ተጠንቀቁ፤ ክፋትን ከሚያደርጉና ሥጋን ከሚቈራርጡ ሰዎች ተጠበቁ።
3 እኛ በእውነት የተገረዝን በእግዚአብሔር መንፈስ የምናመልክ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የምንመካ፣ በሥጋም የማንታመን ነንና።
4 ካስፈለገ እኔም በሥጋ የምመካበት አለኝ።ማንም በሥጋ የሚመካበት ነገር ያለው ቢመስለው፣ እኔ እበልጠዋለሁ፤
5 በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ፣ ከእስራኤል ዘር፣ ከብንያም ወገን የተወለድሁ ስሆን፣ ከዕብራውያንም ዕብራዊ ነኝ፤ ስለ ሕግ ከተነሣ፣ ፈሪሳዊ ነበርሁ፤
6 ስለ ቅናት ከሆነ፣ የቤተ ክርስቲያን አሳዳጅ ነበርሁ፤ ሕግን በመፈጸም ስለ ሚገኝ ጽድቅ ከሆነም፣ ያለ ነቀፋ ነበርሁ።
7 ነገር ግን ይጠቅመኝ የነበረውን ሁሉ አሁን ለክርስቶስ ስል እንደ ጒድለት ቈጥሬዋለሁ።