ፊልጵስዩስ 2 NASV

ትሕትናን ከክርስቶስ መማር

1 ከክርስቶስ ጋር ካላችሁ አንድነት የተነሣ የትኛውም መበረታታት፣ ከፍቅር የሆነ መጽናናት፣ የመንፈስ ኅብረት፣ ምሕረትና ርኅራኄ ካላችሁ፣

2 በአንድ ሐሳብ፣ በአንድ ፍቅር፣ በአንድ መንፈስና በአንድ ዐላማ በመሆን፣ ደስታ ዬን ፍጹም አድርጉልኝ።

3 ሌሎች ከእናንተ እንደሚሻሉ በትሕትና ቊጠሩ እንጂ፣ በራስ ወዳድነት ምኞት ወይም ከንቱ ውዳሴ ለማግኘት አንዳች አታድርጉ።

4 እያንዳንዳችሁ ሌሎችን የሚጠቅመውንም እንጂ፣ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ።

5 በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ያ አስተሳሰብ፣ በእናንተም ዘንድ ይሁን፤

6 እርሱ በባሕርዩ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን ሊለቀው እንደማይገባ አድርጎ አልቈጠረውም፤

7 ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ፣በሰውም አምሳል ተገኝቶ፣ራሱን ባዶ አደረገ፤

8 ሰው ሆኖ ተገልጦም፣ራሱን ዝቅ አደረገ፤እስከ ሞት፣ ያውም በመስቀል ላይ እስከመሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ።

9 ስለዚህ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ አደረገው፤ከስምም ሁሉ በላይ የሆነውን ስም ሰጠው፤

10 ይኸውም በሰማይና በምድር፣ ከምድርም በታች፣ጒልበት ሁሉ ለኢየሱስ ስም ይንበረከክ ዘንድ፣

11 ምላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር፣ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።

እንደ ከዋክብት ማብራት

12 ስለዚህ፣ ወዳጆቼ ሆይ፤ ሁልጊዜም ታዛዦች እንደ ነበራችሁ ሁሉ፣ አሁንም እኔ በአጠገባችሁ ሳለሁ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንም አሁን በሌለሁበት ጊዜ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤

13 እንደ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና።

14 ማንኛውንም ነገር ሳታጒረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ፤

15 ይኸውም በጠማማና በክፉ ትውልድ መካከል ንጹሓንና ያለ ነቀፋ፣ ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች ሆናችሁ፣ እንደ ከዋክብት በዓለም ሁሉ ታበሩ ዘንድ ነው።

16 የሕይወትንም ቃል ስታቀርቡ፣ በከንቱ እንዳልሮጥሁ ወይም በከንቱ እንዳልደከምሁ በክርስቶስ ቀን የምመካበት ይሆንልኛል።

17 ነገር ግን በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ላይ እንደ መጠጥ ቊርባን ብፈስ እንኳ ከሁላችሁ ጋር ደስ ይለኛል፤ ሐሤትም አደርጋለሁ።

18 እናንተም እንደዚሁ ከእኔ ጋር ደስ ልትሰኙና ሐሤት ልታደርጉ ይገባል።

ጢሞቴዎስና አፍሮዲጡ

19 ስለ እናንተ ሰምቼ ደስ እንዲለኝ፣ ጢሞቴዎስን ቶሎ ወደ እናንተ ልልክላችሁ በጌታ ኢየሱስ ተስፋ አደርጋለሁ።

20 ስለ እናንተ ደኅንነት ከልቡ የሚገደው እንደ እርሱ ያለ ማንም የለኝም፤

21 ሁሉም የኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ይሯሯ ጣሉና።

22 ነገር ግን እንደምታውቁት ጢሞቴዎስ ማንነቱን አስመስክሮአል፤ ልጅ ከአባቱ ጋር እንደሚያገለግል፣ ከእኔ ጋር በወንጌል ሥራ አገልግሎአልና።

23 እንግዲህ የራሴን የወደ ፊት ሁኔታ እንዳጣራሁ ልልከው ተስፋ አደርጋለሁ።

24 እኔም ራሴ ቶሎ እንደምመጣ በጌታ ታምኛለሁ።

25 እንዲሁም ወንድሜን፣ የሥራ ባለደረባዬንና አብሮኝ ወታደር የሆነውን፣ በሚያስፈልገኝ ሁሉ እንዲንከባከበኝ የላካችሁትን፣ የእናንተ መልእክተኛ የሆነውን አፍሮዲጡን መልሼ እንድልክላችሁ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

26 እርሱ ሁላችሁንም ይናፍቃልና፤ መታመሙን ስለ ሰማችሁም ተጨንቆአል።

27 በርግጥም ታሞ ለሞት ተቃርቦ ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ምሕረት አደረገለት፤ በሐዘን ላይ ሐዘን እንዳይደራረብብኝ፣ ለእኔም ጭምር እንጂ ለእርሱ ብቻ አይደለም።

28 ስለዚህ እርሱን እንደ ገና ስታዩ ደስ እንዲላችሁና የእኔም ጭንቀት እንዲቀል ልልከው በጣም ጓጒቻለሁ።

29 በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፤ እንደ እርሱ ያሉትንም ሰዎች አክብሯቸው።

30 እርሱም እናንተ ልትሰጡኝ ያልቻላችሁትን አገልግሎት ለማሟላት ሲል ለሕይወቱ እንኳ ሳይሳሳ፣ ለክርስቶስ ሥራ ከሞት አፋፍ ደርሶ ነበርና።

ምዕራፎች

1 2 3 4