5 እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት፣ እንደ ጌታ ወንድሞችና እንደ ኬፋ ሁሉ፣ እኛስ አማኝ ሚስት ይዘን የመዞር መብት የለንምን?
6 ወይስ ጥረን ግረን መኖር ያለብን እኔና በርናባስ ብቻ ነን?
7 ለመሆኑ በገዛ ገንዘቡ በወታደርነት የሚያገለግል ማን ነው? ወይን ተክሎ ፍሬውን የማይበላ ማን ነው? መንጋ እየጠበቀ የከብቱን ወተት የማይጠጣ ማን ነው?
8 ይህን የምናገረው እንደ ሰው አስተሳሰብ ነውን? የኦሪትስ ሕግ ይህንኑ ይል የለምን?
9 በሙሴ ሕግ፣ “የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሰር” ተብሎ ተጽፎአልና። ለመሆኑ፣ እግዚአብሔርን ያሳሰበው የበሬ ጒዳይ ነውን?
10 ይህን የተናገረው በርግጥ ስለ እኛ አይደለምን? የተጻፈው በትክክል ስለ እኛ ነው፤ ዐራሹ የሚያርሰው፣ አበራዩ የሚያበራየው ከምርቱ ድርሻ እንዳለው ተስፋ በማድረግ ነውና።
11 እኛ በእናንተ መካከል መንፈሳዊ ዘር ዘርተን ከሆነ ለሥጋ የሚሆን ነገር ብናጭድ ትልቅ ነገር መሆኑ ነውን?