9 እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ፣ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ ናችሁ።
10 ቀድሞ የእርሱ ወገን አልነበራችሁም፤ አሁን ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆናችኋል፤ ቀድሞ ምሕረትን አላገኛችሁም ነበር፤ አሁን ግን ምሕረትን አግኝታችኋል።
11 ወዳጆች ሆይ፤ በዚህ ዓለም እንግዶችና መጻተኞች እንደመሆናችሁ መጠን፣ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት እንድትርቁ እለምናችኋለሁ።
12 ምንም እንኳ ክፉ እንደምትሠሩ አድርገው ቢያሟችሁም ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ መልካሙን ሥራችሁን ዐይተው እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ፣ በአሕዛብ መካከል በመልካም ሕይወት ኑሩ።
13 ስለ ጌታ ብላችሁ ለምድራዊ ባለ ሥልጣን ሁሉ ተገዙ፤ የበላይ ባለ ሥልጣን ስለ ሆነ ለንጉሥ ቢሆን፣
14 ወይም ክፉ አድራጊዎችን ለመቅጣት፣ በጎ አድራጊዎችን ለማመስገን እርሱ ለሾማቸው ገዦች ታዘዙ፤
15 ምክንያቱም፣ መልካም በማድረግ የአላዋቂዎችን ከንቱ ንግግር ዝም እንድታሰኙ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው።