1 እንግዲህ፣ ወዳጆች ሆይ፤ ይህ የተስፋ ቃል ስላለን፣ ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እግዚአብሔርንም በመፍራት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርገው።
2 ልባችሁን አስፉልን፤ እኛ ማንንም አልበደልንም፤ ማንንም ወደ ብልሹነት አልመራንም፤ ማንንም አላታለልንም።
3 ይህን የምለው ልኰንናችሁ አይደለም፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት እንደ ነገርኋችሁ፣ በልባችን ውስጥ ስፍራ አላችሁ፤ ስለዚህ ብንኖርም ብንሞትም አብረን ነው።
4 በእናንተ ላይ ያለኝ እምነት ትልቅ ነው፤ በእናንተም ላይ ያለኝ ትምክሕት ትልቅ ነው፤ እንዲሁም እጅግ ተጽናንቻለሁ፤ በመከራችንም ሁሉ ደስታዬ ወሰን የለውም።
5 ወደ መቄዶንያ በመጣን ጊዜ ከየአቅጣጫው መከራ ደረሰብን እንጂ ሰውነታችን ዕረፍት አላገኘም፤ ከውጭ ጠብ፣ ከውስጥ ደግሞ ፍርሀት ነበረብን።
6 ይሁን እንጂ ሐዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን።
7 የተጽናናነውም በመምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ እርሱንም ልታጽናኑት በመቻላችሁ ጭምር ነው። ስለ ናፍቆታችሁ፣ ስለ ሐዘናችሁና ለእኔም ስላላችሁ ቅናት ነግሮናል፤ ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ደስ ብሎኛል።