1 በተራራማው በኤፍሬም አገር በአርማቴም መሴፋ የሚኖር ሕልቃና የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ እርሱም ኤፍሬማዊ ሲሆን፣ የኤያሬምኤል ልጅ፣ የኢሊዩ ልጅ፣ የቶሑ ልጅ፣ የናሲብ ልጅ፣ ነበረ።
2 እርሱም አንዲቱ ሐና፣ ሌላዪቱ ፍናና የተባሉ ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ ፍናና ልጆች ሲኖሯት፣ ሐና ግን ምንም ልጅ አልነበራትም።
3 ያም ሰው ሁሉን ቻይ ለሆነው ለእግዚአብሔር ለመስገድና መሥዋዕት ለመሠዋት በየዓመቱ ከሚኖርበት ከተማ ወደ ሴሎ ይወጣ ነበር። በዚያም ሁለቱ የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ የእግዚአብሔር ካህናት ነበሩ።
4 ሕልቃና ወደ ሴሎ ሄዶ መሥዋዕት የሚሠዋበት ወቅት በደረሰ ጊዜ ሁሉ፣ ለሚስቱ ለፍናና እንዲሁም ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቿ ሁሉ ከሥጋው ድርሻቸውን ይሰጣቸው ነበር።