1 ሳሙኤል 1:8-14 NASV

8 ባሏ ሕልቃናም እርሷን፣ “ሐና ሆይ፤ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበዪም? ልብሽስ ለምን ያዝናል? ከዐሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽምን?” ይላት ነበር።

9 አንድ ጊዜ በሴሎ ሳሉ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ሐና ተነሥታ ቆመች፤ በዚያ ጊዜ ካህኑ ዔሊ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መቃን አጠገብ በወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር።

10 ሐናም በነፍሷ ተመርራ አብዝታ በማልቀስ ወደ እግዚአብሔር ጸለየች።

11 እንዲህም ብላ ስእለት ተሳለች፤ “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአገልጋይህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝና አገልጋይህን ሳትረሳት ወንድ ልጅ ብትሰጣት፣ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፤ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም።”

12 ሐና ባለማቋረጥ ወደ እግዚአብሔር በጸለየች ጊዜ፣ ዔሊ አፏን ይመለከት ነበር።

13 እርሷም በልቧ ትጸልይ ስለ ነበር፤ ከንፈሯ ይንቀሳቀስ እንጂ ድምጿ አይሰማም ነበር፤ ዔሊም እንደ ሰከረች አድርጎ ቈጠራት።

14 እርሱም “ስካሩ የማይለቅሽ እስከ መቼ ድረስ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አስወግጂው” አላት።