1 ሳሙኤል 10:18-24 NASV

18 እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እስራኤልን ከግብፅ አወጣሁት፤ ከግብፃውያን እጅ ይጨቁኗችሁ ከነበሩት ከሌሎቹ መንግሥታት ሁሉ እጅ ታደግኋችሁ።”

19 ዛሬ ግን ከመከራችሁና ከጭንቃችሁ ሁሉ የሚያድናችሁን አምላካችሁን ንቃችሁ፤ ‘የለም፤ ንጉሥ አንግሥልን’ አላችሁ። ስለዚህ በየነገዳችሁና በየጐሣችሁ ሆናችሁ በእግዚአብሔር ፊት ቅረቡ።”

20 ሳሙኤል የእስራኤልን ነገዶች ሁሉ ባቀረበ ጊዜ፣ የብንያም ነገድ ተመረጠ።

21 ከዚያም የብንያምን ነገድ በየጐሣው ወደ ፊት አቀረበ፤ የማጥሪ ጐሣም ተመረጠ። በመጨረሻም የቂስ ልጅ ሳኦል ተመረጠ። እርሱ ግን ተፈልጎ አልተገኘም።

22 ሰዎቹም፣ “ሰውየው መጥቶአልን?” ሲሉ እግዚአብሔርን ጠየቁ። እግዚአብሔርም፣ “አዎን፤ ነገር ግን በዕቃ መካከል ተሸሽጎአል” አለ።

23 እነርሱም ሮጠው ከተደበቀበት አመጡት፤ በሕዝቡ መካከል በቆመ ጊዜም ቁመቱ ከሌሎቹ ሁሉ ይልቅ ከትከሻው በላይ ዘለግ ያለ ነበር።

24 ሳሙኤልም መላውን ሕዝብ፣ “እግዚአብሔር የመረጠውን ሰው አያችሁን? ከሕዝቡ ሁሉ የሚስተካከለው ማንም የለም” አለ።ከዚያም ሕዝቡ፣ “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!” ብሎ ጮኸ።