1 ሳሙኤል 11:3-9 NASV

3 የኢያቢስም ሽማግሌዎች፣ “ወደ መላው እስራኤል መልእክተኞችን እንድንልክ የሰባት ቀን ጊዜ ስጠን፤ ሊታደገን የሚመጣ ሰው ከሌለ፣ ለአንተ እንገዛለን” አሉት።

4 መልእክተኞቹም ሳኦል ወዳለበት ወደ ጊብዓ መጥተው ይህን ለሕዝቡ በተናገሩ ጊዜ፣ ሕዝቡ ሁሉ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤

5 በዚህ ጊዜ፣ ሳኦል በሬዎቹን እየነዳ ከዕርሻ ተመለሰ፤ እርሱም፣ “ሕዝቡ የሚያለቅሰው ምን ሆኖ ነው?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም የኢያቢስ ሰዎች ያሏቸውን ነገሩት።

6 ሳኦል ይህን በሰማ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ እጅግ ተቈጣ።

7 ጥንድ በሬዎች ወስዶ ቈራረጠ፤ ሥጋቸውንም በመልእክተኞች እጅ ልኮ፣ “ሳኦልንና ሳሙኤልን የማይከተል ሰው በሬው እንደዚህ ይቈራረጣል” ሲል በመላው እስራኤል አስነገረ። ታላቅ ፍርሀት ከእግዚአብሔር ዘንድ በሕዝቡ ላይ ወደቀ፤ ሕዝቡም እንደ አንድ ሰው ሆኖ ወጣ።

8 ሳኦል ቤዜቅ በተባለ ስፍራ ሰራዊቱን በሰበሰበ ጊዜ፤ ቊጥራቸው ከእስራኤል ሦስት መቶ ሺህ፣ ከይሁዳም ሠላሳ ሺህ ነበር።

9 ከዚያ ለመጡትም መልእክተኞች፣ “ለኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች፣ ‘ነገ ፀሓይ ሞቅ በሚልበት ጊዜ ነጻ ትሆናላችሁ’ ብላችሁ ንገሯቸው” አሏቸው። መልእክተኞቹም ሄደው ለኢያቢስ ሰዎች ይህንኑ በነገሯቸው ጊዜ በደስታ ፈነደቁ።