1 ሳሙኤል 12:12-18 NASV

12 የአሞናውያን ንጉሥ ናዖስ እንደ መጣባችሁ ባያችሁ ጊዜ ግን፣ ምንም እንኳ አምላካችሁ እግዚአብሔር ንጉሣችሁ ቢሆንም፣ ‘አይሆንም፤ የሚገዛን ንጉሥ እንፈልጋለን’ አላችሁ።

13 “አሁንም የጠየቃችሁትና የመረጣችሁት ንጉሥ ይኸው፤ እነሆ፣ እግዚአብሔር በላያችሁ ንጉሥ አንግሦአል።

14 እግዚአብሔርን የምትፈሩና የምታመልኩ፣ የምትታዘዙትና በትእዛዛቱ ላይ የማታምፁ ከሆነ፣ እንዲሁም እናንተና በእናንተ ላይ የነገሠው ንጉሥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ከተከተላችሁ መልካም ይሆንላችኋል።

15 እግዚአብሔርን የማትታዘዙና በትእዛዛቱም ላይ የምታምፁ ከሆነ ግን፣ እጁ በአባቶቻችሁ ላይ እንደ ነበረች ሁሉ በእናንተም ላይ ትሆናለች።

16 “ስለዚህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር በዐይናችሁ ፊት የሚያደርገውንም ይህን ታላቅ ነገር ተመልከቱ፤

17 አሁን የስንዴ መከር ጊዜ አይደለምን? እኔ ነጐድጓድና ዝናብ እንዲልክ ወደ እግዚአብሔር እጮኻለሁ፤ እናንተም ንጉሥ እንዲነግሥላችሁ በመጠየቃችሁ በእግዚአብሔር ፊት የቱን ያህል የከፋ ድርጊት እንደፈጸማችሁ ያን ጊዜ ታውቃላችሁ።”

18 ከዚህ በኋላ ሳሙኤል ወደ እግዚአብሔር ጮኸ፤ በዚያኑ ዕለት እግዚአብሔር ነጐድጓድና ዝናብ ላከ። ስለዚህ ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርንና ሳሙኤልን እጅግ ፈሩ።