1 ሳሙኤል 13:1-6 NASV

1 ሳኦል በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበረ፤ እስራኤልንም አርባ ሁለት ዓመት ገዛ።

2 ሳኦል ከእስራኤል ሦስት ሺህ ሰዎች መረጠ። ሁለቱ ሺህ በማክማስና በኰረብታማው አገር በቤቴል ከሳኦል ጋር፣ አንዱ ሺህ ደግሞ በብንያም ግዛት በጊብዓ ከዮናታን ጋር ነበሩ። የቀሩትን ሰዎች ግን ወደ የቤታቸው እንዲሄዱ አሰናበተ።

3 ዮናታን ጊብዓ የነበረውን የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር መታ፤ ፍልስጥኤማውያንም ይህን ሰሙ። ሳኦልም፣ “ዕብራውያን ይስሙ!” በማለት በምድሪቱ ሁሉ መለከት አስነፋ።

4 ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ፣ “ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጦር ሰፈር መታ፤ እስራኤልም በፍልስጥኤማውያን ዘንድ እንደ ርኩስ ተቈጥራ ተጠላች” የሚለውን ወሬ ሰሙ፤ ሕዝቡም ሳኦልን ለመከተል ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ።

5 ፍልስጥኤማውያን ሦስት ሺህ ሠረገሎች፣ ስድስት ሺህ ፈረሰኞች ቊጥሩ እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ ሰራዊት ይዘው እስራኤልን ለመውጋት ተሰበሰቡ፤ ወጥተውም ከቤት አዌን በስተ ምሥራቅ ባለችው በማክማስ ሰፈሩ።

6 እስራኤላውያን፣ ያሉበት ሁኔታ እጅግ የሚያሠጋ መሆኑንና ሰራዊታቸውም በከባድ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን ባዩ ጊዜ፣ በየዋሻውና በየቊጥቋጦው፣ በየዐለቱ መካከልና በየገደሉ እንዲሁም በየጒድጓዱ ሁሉ ተደበቁ።