4 ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ፣ “ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጦር ሰፈር መታ፤ እስራኤልም በፍልስጥኤማውያን ዘንድ እንደ ርኩስ ተቈጥራ ተጠላች” የሚለውን ወሬ ሰሙ፤ ሕዝቡም ሳኦልን ለመከተል ወደ ጌልገላ ተሰበሰቡ።
5 ፍልስጥኤማውያን ሦስት ሺህ ሠረገሎች፣ ስድስት ሺህ ፈረሰኞች ቊጥሩ እንደ ባሕር አሸዋ የበዛ ሰራዊት ይዘው እስራኤልን ለመውጋት ተሰበሰቡ፤ ወጥተውም ከቤት አዌን በስተ ምሥራቅ ባለችው በማክማስ ሰፈሩ።
6 እስራኤላውያን፣ ያሉበት ሁኔታ እጅግ የሚያሠጋ መሆኑንና ሰራዊታቸውም በከባድ ጭንቀት ውስጥ መግባቱን ባዩ ጊዜ፣ በየዋሻውና በየቊጥቋጦው፣ በየዐለቱ መካከልና በየገደሉ እንዲሁም በየጒድጓዱ ሁሉ ተደበቁ።
7 ከዕብራውያንም አንዳንዶቹ ዮርዳኖስን ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር ሄዱ።ሳኦል ግን በጌልገላ ቈየ፣ አብሮት የነበረውም ሰራዊት ሁሉ በፍርሀት ይንቀጠቀጥ ነበር።
8 እርሱም ሳሙኤል በሰጠው ቀጠሮ መሠረት ሰባት ቀን ጠበቀው። ነገር ግን ሳሙኤል ወደ ጌልገላ አልመጣም፤ የሳኦልም ሰራዊት መበታተን ጀመረ።
9 በዚህ ጊዜ ሳኦል፣ “የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕቱን አምጡልኝ” አለ። ከዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ።
10 ልክ መሥዋዕቱን አቅርቦ እንዳበቃ፣ ወዲያውኑ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም ሊቀበለው ወጣ።