1 ሳሙኤል 14:21-27 NASV

21 እነዚያ ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጐን ተሰልፈው የነበሩትና አብረዋቸውም ወደ ሰፈራቸው የወጡት ዕብራውያን ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደ ነበሩት እስራኤላውያን ገቡ።

22 በኰረብታማው የኤፍሬም አገር ተሸሽገው የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ ፍልስጥኤማውያኑ በሽሽት ላይ መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ፣ አጥብቀው በመከታተል አሳደዷቸው።

23 በዚያ ቀን እግዚአብሔር እስራኤልን ታደገው፤ ጦርነቱም ከቤት አዌን ዘልቆ ሄደ።

24 ሳኦል፣ “ዛሬ ጠላቶቼን ከመበቀሌ በፊት እስከ ማታ ድረስ እህል የሚበላ ሰው የተረገመ ይሁን” ብሎ ሕዝቡን አምሎ ስለ ነበር፣ በዚያች ዕለት የእስራኤል ሰዎች ተጨንቀው ዋሉ፤ ስለዚህ ከሕዝቡ አንድም እህል የቀመሰ አልነበረም።

25 ሰራዊቱ ሁሉ ወደ ጫካ ሲገባ፣ ማር በመሬቱ ላይ ይታይ ነበር።

26 ሕዝቡ ወደ ጫካው በገባ ጊዜ፣ የማሩ ወለላ እየተንጠባጠበ መውረዱን አየ፤ ሆኖም መሓላውን ፈርቶ ስለ ነበር፣ እጁን ወደ አፉ የዘረጋ ማንም አልነበረም።

27 ነገር ግን ዮናታን አባቱ ሕዝቡን በመሐላ ማሰሩን አልሰማም ነበር። ስለዚህ በእጁ የያዘውን ዘንግ ጫፍ በማሩ ወለላ ውስጥ በማስገባት እጁን ወደ አፉ አደረገ፤ ዐይኑም በራ።